ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላችንን እንወጣለን- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ጋምቤላ፣ጥቅምት16/2019 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላችንን እንወጣለን ሲል የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ መግለጫ ሰጥቷል።

የጋራ የምክር ቤቱ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ጋድቤል ቦል፤ በሰላምና በልማት ጉዳይ ላይ ከመንግስት ጋር በጋራ እየሰራን እንገኛለን በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ የአይዲዮሎጂ፣ የፖሊሲና የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖረንም በልማት፣ በዘላቂ ሰላም ግንባታ እንዲሁም የህዝብን ጥቅም በማስቀጠል ረገድ የጋራ አቋም አለን ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም በጋምቤላ ክልል ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ በክልሉ የሰላም፣ የልማት እንዲሁም የህዝቡን ተጠቃሚነት በማስቀጠል ረገድ ጠንካራ አቋም ይዞ ይሰራል ብለዋል።

የጋራምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢና የህዳሴ ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ተጠሪ ሻምበል ቶላ በበኩላቸው የህግ የበላይነትንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት ለሚያደርጋቸው ጥረቶች የጋራ ምክር ቤቱ የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ብለዋል። 

የጋምቤላ ክልል እምቅ የመልማት አቅም ያለው መሆኑን ገልጸው የኢኮኖሚ ማንሰራራትን፣ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ጸሀፊና በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንፃጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፔን ኡጁሉ፤ በክልሉ ያለውን የልማት አቅም ወደ ውጤት በመቀየር ብሎም የሰላም እሴት ግንባታን ለማጠናከር ይበልጥ ተቀራርበን እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም