ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በሰብዓዊ ጉዳዮች ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከኮሚቴው የአፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ማማዱ ሶው እና ልዑካቸው ጋር ተወያይተዋል።


 

ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ላላት የረጅም ጊዜ አጋርነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከኮሚቴው ጋር በሰብዓዊ ጉዳዮች ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) የአፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ማማዱ ሶው ለኢዜአ እንዳሉት፣ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ አስፈላጊነት እና በሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች ዙሪያ ከፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን ማስከበርና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ማኅበረሰቦችን ለመደገፍ የመሪዎችን ቁርጠኝነትና የተቋማትን ትብብር እንደሚጠይቅ አንስተዋል።

ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የሥራ ተደራሽነትና ተቀባይነት ለሰብዓዊ ተልዕኮው መሳካት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከርም የኮሚቴው ሌላው ትኩረት መሆኑን አመልክተዋል።

ሁለቱ ተቋማት በመላ ሀገሪቱ በውኃ አቅርቦት፣ በጤናና በምግብ ዋስትና ዘርፎች በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለቀይ መስቀል ማኅበር ለምታደርገው ድጋፍም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም