ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት በአካልና በአዕምሮ የበለጸገ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ መሰረት ጥሏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነትን በማረጋገጥ በአካልና በአዕምሮ የበለጸገ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ የምርታማነት መሰረት መጣሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በዓርባ ምንጭ ከተማ የተበሰረው "የሌማት ትሩፋት" መርሃ ግብር የግብርና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እያሻሻለ ይገኛል።

መርሃ ግብሩም የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የዓሳና የንብ ማነብ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት አቅምን በማሳደግ በሀገሪቱ የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነት ላይ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ቀጥሏል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አዚዝ አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የእንስሳት፣ የዓሳ፣ የንብና የፍራፍሬ ልማት ዘርፍ የሚገባውን ያህል ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋትም የዘርፉን የዘፈቀደ የአመራረት ሥርዓት በማላቀቅ ዘመናዊ የምርታማነት ምኅዳር እንዲጎናጸፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ከ2015 እስከ 2018 ዓ.ም በተተገበረው የመጀመሪያው ዙር አራት ዓመታት የልማት ዕቅድ ዘመናዊ አሰራርን በማበረታታት በሁሉም ዘርፎች እምርታዊ የምርት እድገት ማምጣት መቻሉን አብራርተዋል።

በዚህም የዶሮና እንቁላል፣ የወተትና ሥጋ፣ የማርና ዓሣ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት የአርሶና አርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

ይህም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የገበያ የምርት አቅርቦትን በመደገፍ የገቢ ምንጫቸውን በማስፋት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በዓይነትና በጥራት የበለጸገ ብዝኅ የምግብና የሥነ-ምግብ ሥርዓትን በመፍጠር በአካልና በአዕምሮ የበለጸገ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።

መርሃ-ግብሩ ሀገራዊ የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ አወንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተያዙ የግብርና ምርታማነት ዘርፎችም ከዓመታት በፊት ከነበሩበት የዘፈቀደ የአመራረት ሥርዓት በመላቀቅ ከፍተኛ የምርት አቅም መፍጠር እንዳስቻሉ አንስተዋል።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ዘመናዊ የምርታማነት ምኅዳርን በማበረታታት በሁሉም ዘርፎች በብዙ እጥፍ እምርታዊ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በቀጣይም የዘርፉን ምርታማነት በዘመናዊ አሰራርና ቴክኖሎጂ በማላቅ የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመጀመሪያው ዙር የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት በማስቀጠል ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማላቅ 2ኛው ዙር የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ትግበራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ለአብነትም በ2019 በጀት ዓመት 18 ቢሊዮን ሊትር ወተት፣ 14 ነጥብ 6 ቢሊዮን እንቁላል፣ 400 ሺህ ቶን የዓሳ እና 489 ሺህ ቶን የማር ምርት ለማግኘት ታቅዶ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ  መሆኑን ጠቁመዋል።

የተያዘውን አገራዊ ዕቅድ ለማሳካትም የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርታማነት የሚያስፈልጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችና ቅንጅታዊ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ትግበራ መገባቱን አረጋግጠዋል።

ሁለተኛውን የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ዕቅድም የመጀመሪያውን የዕቅድ አፈጻጸም በተሻለ አቅምና ጥራት በማላቅ ከ2019 ዓ.ም እስከ 2021 ዓ.ም በሶስት ዓመታት እንደሚተገበር አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም