ቀጥታ፡

ጣና ፎረም : ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካውያን መፍትሔ በተግባር የተገለጠበት አህጉራዊ መድረክ

ጣና ፎረም መነሻ መሠረቱ በነሐሴ ወር 2001 ዓ.ም በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ልዩ የመሪዎች ስብሰባ ላይ የፀደቀው ታሪካዊው የትሪፖሊ መግለጫ ነው።

ይህ አህጉራዊ የፖሊሲ ሰነድ በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት "ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካውያን መፍትሔ" (African-led solutions) የሚለውን መርህ ያስቀመጠ ሲሆን፣ የሰላም ግንባታው በምሁራንና በሲቪል ማኅበራት እውቀት ጭምር መደገፍ እንዳለበት ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ይህንን አቅጣጫ በተግባር ለመተርጎም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም (IPSS) ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በመተባበር መሪዎችና ምሁራን በነፃነት የሚወያዩበትን የጣና ፎረም በ2004 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በይፋ አስጀምሯል።

ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ የጣና ፎረም የአፍሪካን ወቅታዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የደህንነት ስጋቶች እየገመገመ በርካታ ስኬታማ ጉባኤዎችን አካሂዷል።

ከመደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ፕሮቶኮሎች ወጣ ባለ መልኩ፣ መሪዎች በግልጽና በነፃነት እንዲወያዩ ምቹ መድረክ ፈጥሯል።

ሀሳብ በነጻነት መንሸራሸሩ ልዩ መገለጫው እንደሆነ ደጋግሞ ይነሳል።

ፎረሙ በርካታ የሀገራት መሪዎችና የቀድሞ መሪዎች፣ ምሁራን፣ የወጣት ተወካዮችና የሲቪል ማኅበራትን በማሳተፍ በአህጉሪቱ ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ የፖሊሲ አማራጮችን ሲያመነጭ ቆይቷል።

ይህ አህጉራዊ መድረክ በሂደቱ ለአፍሪካ አዳዲስ ዲፕሎማሲያዊና ስትራቴጂካዊ ዕድሎችን በሰፊው መፍጠር ችሏል።

መድረኩ በተለይም ወጣት አፍሪካውያን ምሁራንና ተመራማሪዎች ከአህጉሪቱ ከፍተኛ መሪዎች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙና ሐሳቦቻቸውን እንዲያካፍሉ በር ከፍቷል።

ይህ መስተጋብር በአፍሪካ የሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ አዲስና ተራማጅ አስተሳሰብ እንዲሰርጽ ከማድረጉም በላይ፣ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ወጥ የሆነና ጠንካራ የጋራ አቋም እንድትይዝ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።


 

ፎረሙ ዘንድሮም 12ኛውን አህጉራዊ ጉባኤውን በባህር ዳር ከተማ ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ አካሂዷል።

የዘንድሮው ጉባኤ “አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የቀጣናዊ ፖለቲካዊ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ ላይ ያተኮረ ነው።

ፎረሙ በአፍሪካ ቀንድና በመላው አህጉሪቱ እየታዩ ያሉትን የጂኦፖለቲካ ፉክክሮች፣ የሽብርተኝነት ስጋት እና የኢኮኖሚ ጫናዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ እውቀት-ተኮር መፍትሔዎች ቀርበውበታል።

የጣና ፎረም ቀጣይ ግብ አፍሪካ በዓለም አቀፉ መድረክ ላይ ያላትን የዲፕሎማሲና የድርድር አቅም ማሳደግ እና በራሷ እግር እንድትቆም ማስቻል ነው።

ፎረሙ ከቀውስ አስተዳደር ባለፈ፣ ዘላቂ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መዋቅሮችን በመገንባት የአፍሪካ ኅብረትን የአጀንዳ 2063 ራዕይ የማሳካት ውጥን አለው።


 

በተጨማሪም፣ የመነጩ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦች በተግባር ላይ እንዲውሉ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችን ማጠናከርና የአፍሪካን ድምፅ በዓለም አቀፍ የሰላምና ደኅንነት ሥነ-ምህዳር ውስጥ ይበልጥ ተሰሚ ማድረግ ዋነኛ የረጅም ጊዜ ግቡ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም