ቀጥታ፡

በሀገሪቱ የተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ስልጠና ውጤታማነትና ለተግባራዊ እውቀት ሽግግር ትልቅ ዕድል ፈጥረዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ስልጠና ውጤታማነትና ለተግባራዊ እውቀት ሽግግር ትልቅ ዕድል መፍጠራቸውን የኢትዮጵያ የቴክኒክ ልህቀት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ የቴክኒክ ልህቀት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት የተተገበሩት የስልጠና ፕሮግራሞች ለክህሎት ማደግ ከፍተኛ ትኩረት የሰጡና የወጣቶችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ናቸው።

ይህም የገበያውን ክፍተት የሚሞሉ አዳዲስ የሙያ ዘርፎችን በማካተት ለቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ውጤታማነት  አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የዲጂታል ዘመኑን እና ቴክኖሎጂውን ፍላጎት ለማሟላት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ ሮቦቲክስ፣ ባዮሜዲካል እና የኒው ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ዘመኑን የዋጁ አጫጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ሰልጣኞች ከተቋሙ ከሚያገኙት ተግባር ተኮር ትምህርት ባለፈ በኢንዱስትሪዎች ያለውን ጠቃሚ ተሞክሮ እንዲቀስሙ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ ስራ እየተከናወነ ነው።

ተቋሙ ከ170 በላይ ልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በመፈራረም በኢነርጂ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በቱሪዝም እና በማዕድን ዘርፎች በክህሎትና በእውቀት የዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት በቅርበት እየሰራ ይገኛል።

በተጨማሪም የሀገሪቱን ልማት ለማፋጠን ኢንስቲትዩቱ ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶች የሚሰሩበት ምህዳር ለመፍጠር "ስኪል ኢትዮጵያ" በሚል ኢንሼቲቭ እየተንቀሳቀሰ መቆየቱን ተናግረዋል።

የሀገሪቱን ልማት ለማፋጠን "ስኪል ኢትዮጵያ" የተሰኘው ኢንሼቲቭ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶች የሚፈጠሩበት ምህዳር በመፍጠር በኩል ትልቅ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

ኢንሼቲቩ የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰልጣኞች በመደገፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በግብርና፣ በአይሲቲ እና በማዕድን ዘርፎች 99 የሚደርሱ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማስገኘቱን አንስተዋል። 

እንደ ማሳያነት በግብርናው ዘርፍ ከተጠቀሱት ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ የገጠር ኮሪደር ልማትን ለማፋጠን የሚያግዙ የብሪክስ ማኑዋል እና የሀይድሮሊክ ማሽኖች በብዛት ተመርተው ለክልሎች ተደራሽ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የስልጠና ማዕከላት ውጤታማነት ለማጎልበት የአካባቢን ጸጋና አቅም መሰረት ያደረጉ ፕሮግራሞች እየተከፈቱ መሆኑ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ የተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ስልጠና ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም ነው የገለጹት። 

ኢንስቲትዩቱ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማፋጠን ረገድ የቴክኒክና ሙያ መስኩ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አንስተዋል። 

ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር በሀገር ውስጥ መተካት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን የመፍጠር ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉንም ተናግረዋል።

በዚህም በየደረጃው ብቁና ተወዳዳሪ ሰልጣኞችን በማፍራት የሀገሪቱን የልማት ጉዞ የማፋጠን ድርሻውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም