በክልሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ የማድረግ ስራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ የማድረግ ስራ ይጠናከራል
ቦንጋ ፣ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ተግባር አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት ውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል ።
የቢሮው ሀላፊ አቶ እንዳሻው ከበደ በወቅቱ እንደገለፁት በክልሉ መንግስታዊ አገልግሎቶችን በማዘመን ፈጣንና ቀልጣፋ ከማድረግ ጎን ለጎን ተደራሽ የማድረግ ስራ ይጠናከራል።
በክልሉ በስድስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በዚህም የተገልጋዩ እርካታ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በማዕከላቱ 45 ተቋማት 231 አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው በእስካሁኑ ሂደት 63 ሺህ 960 ተገልጋዮች አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት አመትም ተጨማሪ 15 ማዕከላትን በመገንባት ወደ ስራ የማስገባት እንዲሁም የሚሰጡ አገልግሎቶችንም የማስፋት ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል ።
ከዘሁ ጎን ለጎን የመንግስት ተቋማትን በተገቢው የሰው ሀይል በማደራጀትና የሰራተኞችን አቅም በመገንባት የአገልግሎቶችን ጥራትና ቅልጥፍና የማሻሻል ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።
በመድረኩም ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበት የታዩ ክፍተቶችን በማረም የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ አቅምን ለመገንባት ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።