በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመስኖ ልማት የአርሶ አደሮችን ምርታማነትና የገቢ አቅም እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመስኖ ልማት የአርሶ አደሮችን ምርታማነትና የገቢ አቅም እያሳደገ ነው
አሶሳ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ):- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመስኖ ልማት ምርታማነታቸውና የገቢ አቅማቸው እያደገ መሆኑን በክልሉ የአቡራሞ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በክልሉ አቡራሞ ወረዳ የቡልድገሉ ቀበሌ አርሶ አደር አልፋድል አሳቢር፤ በመስኖ በኩታገጠም በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ምርታማነታቸውና የገቢ አቅማቸው እያደገ በመሆኑ ከቤተሰባቸው አልፎ ለገበያ በማቅረብ የገቢ አቅማቸውን እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳው በመስኖ ልማት ላይ የተሰማሩት አርሶ አደር ሲቱ ደፋአላ፤ የመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፎ በህይወታቸው ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ይናገራሉ።
በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ሽንኩርትና ሌሎችንም በስፋት የማልማት እቅድ ይዘው እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር መንሱር መርዙቅ፤ የመስኖ ልማት ስራ የምርት አማራጭን የሚያሰፋና የገቢ አቅም የሚያሳድግ በመሆኑ ይህንኑ በመረዳት በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የአቡራሞ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታላይ ደረጀ፤ በወረዳው የመስኖ ልማት በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ከ9 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እቅድ ተይዞ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በርካታ አርሶ አደሮችም በኩታ ገጠም የመስኖ ስራ ላይ አተኩረው እየሰሩ መሆኑን አንስተው፤ አዳዲስ የመስኖ ቦታዎችን በመለየት ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ባበክር ሀሊፋ፤ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም እስካሁን ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መሸፈኑን ገልጸው፤ አርሶ አደሩም ለመስኖ ልማት ስራ ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።