ቀጥታ፡

የክልሉን ሀብቶች ለልማት በማዋል የዜጎችን ተጠቃሚነት የማሳደግ ሥራ ይጠናከራል 

ጂንካ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ የክልሉን የተፈጥሮ ሀብቶች ለልማት በማዋል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከአሪ እና ከደቡብ ኦሞ ዞኖች ከተወጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በጂንካ ከተማ ተወያይተዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ላይ የአሪ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች በተፈጥሮ ሀብት የበለጸጉ ከመሆናቸው ባለፈ ሰፊ የግብርና እና የቱሪዝም ሀብት እንዳላቸው ተናግረዋል።

እነዚህን አካባቢዎች ጨምሮ በክልሉ ያሉ ዕምቅ ሀብቶችን ለይቶ በማልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በመደመር መንግሥት ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት እና ለጋራ ብልጽግና ቅድሚያ እንደሚሰጥ የገለጹት ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ በዚህም በልማት ወደኋላ የቀሩ አካባቢዎችንም ጭምር ለማልማት ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በአሪ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለማህበረሰብ ለውጥና ለሀገር  ዕድገት ለማዋል በሚደረገው ጥረት አመራሩ ከምንጊዜም በላይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።


 

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አፌዱ ወርቁ ዞኑ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በኢንቨስትመንት ዕምቅ አቅም አለው ብለዋል። ከኤክስፖርት ምርት ቡና፣ ኮሮሪማ እና የቅመማ ቅመም ምርቶች በስፋት የሚመረትበት መሆኑንም አንስተዋል።

የአሪ ዞን ሰፊ ለም መሬት እና በቂ የውሃ ሀብት ያለው በመሆኑ ይህን እምቅ አቅም በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የግብርና ምርቶች በስፋት በማልማት የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በበኩላቸው፤ ዞኑ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ያሉት፣ የብዘሃነት ማሳያ፣ የተለያዩ ማዕድናት መገኛ እንዲሁም ሰፊ የግብርና አቅም ያለው መሆኑን አንስተዋል።

እነዚህን ሀብቶች ለልማት በማዋል የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመለወጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ የአርብቶ አደሩ የመስኖ ልማት ተሳትፎ እየደገ መምጣቱን የገለጹት አቶ ማዕከል፣ በዚህም አርብቶ አደሩ ተጠቃሚነቱን እያሳደገና ሀብት እያፈራ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም