ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት መርሃ ግብር የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የኒውክሌር ልማት የሚያፋጥን ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን በጎበኙበት ወቅት፤ የኒውክሌር ልማት ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂክ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አቅም በመገንባት የኢንዱስትሪና ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ተቋማዊና ቴክኒካዊ መሰረቶችም የጉባ ብስራቶች የኢትዮጵያን የተትረፈረፈ ጸጋ ወደ ተጨባጭ የልማት ዕድል እየተቀየሩ መሆናቸውን እንደሚያመላክት አንስተዋል።


 

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ጌታቸው አዳም (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ አቅምን የሚያጎለብት የኃይል አማራጭ ነው።

በአሁኑ የዘመናዊ ዓለም የኒውክሌር ልማት ሳይንስና ፈጠራን በማበረታታት የግብርና፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪና ተያያዥ ዘርፎችን የዕድገት ሽግግር በማፋጠን ከፍተኛ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በግብርና ዘርፍም ምርጥ ዘርና ተባይን መከላከል የሚያስችሉ የፈጠራና ምርምር ውጤቶችን በማፍለቅ ምርታማነትን ለማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት መርሃ ግብርም የኃይል አማራጭ አስተማማኝነትን በማጎልበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ሽግግርን ለማፋጠን ዓይነተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያን የግብርና፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች የልማት ዘርፎችን ምርታማነት በማሻሻል የኢንቨስትመንት አቅምን ለማጎልበት እንደሚረዳ ጠቅሰዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የኒውክሌር ማብላያ የልህቀት ማዕከል ኃላፊና ተመራማሪ ደረጃው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኒውክሌር አስተማማኝና የማይቋረጥ ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ልማት መርሃ ግብርም ከአየር ብክለት የጸዳ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለመገንባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የኒውክሌር ልማት መርሃ ግብሩም የጤና፣ ኢንዱስትሪና ግብርና ልማት ውጤታማነትን በማሳደግ የሳይንስና ፈጠራ ሽግግርን ለማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲውም የኢትዮጵያን የኒውክሌር ልማት የሚያሳልጥ ሰው ሃይል ለማፍራት በሁለተኛ ድግሪ የትምህርት መርሃ ግብር ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በመጀመሪያ ድግሪ የኒውክሌር ሳይንስ ትምህርትና ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የኒውክሌር ፕሮግራም የዝግጅት፣ የግንባታ፣ የአወጋገድና ሌሎች ሂደቶች ሙያተኞችን የሚጠይቁ መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም በዩኒቨርሲቲው ለማስተማሪያነት የሚያገለግል የኒውክሌር ሪሰርች ሪአክተር ላቦራቶሪ ግንባታ በማጠናቀቅ የኒውክሌር ማዕከል ተቋቁሞ እየተሰራበት እንደሆነም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን፣ ከሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ቴክኖሎጂውን ለሰላማዊ ዓላማ ለማዋል በበላይነት የሚቆጣጠርና ዘርፉን በብቃት ለመምራት የሚያስችሉ ዕቅዶችንና ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም