በሲዳማ ክልል በማህበር ተደራጅተው በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸው አድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በማህበር ተደራጅተው በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸው አድጓል
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ በሕብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው በቡና ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደጉ መምጣታቸውን ገለጹ፡፡
የወረዳው ሕብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ በወረዳው ከ12 ሺህ 300 በላይ ቡና አምራች አርሶ አደሮች በሕብረት ሥራ ማህበር መደራጀታቸውን አስታውቋል፡፡
በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በሕብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው ከሚያመርቱት ቡና የተሻለ ገቢ በማግኘት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ነው፡፡
በወረዳው የፉራና አካባቢው የሕብረት ሥራ ማህበር አባል አቶ ታምራት ታደሰ እንደገለጹት፤ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ከ3ሺህ 700 ኪሎ ግራም በላይ እሸት ቡና ለማህበሩ አቅርበዋል።
በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ቡና ለማምረት የሚያስችል በቂ ስልጠና ማግኘታቸው ለማህበሩ በየዓመቱ ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለብዙ ዓመታት የሕብረት ሥራ ማህበሩ አባል እንደሆኑ የገለጹት አርሶ አደር ምርጋ ሺላ በበኩላቸው፣ ከሕብረት ሥራ ማህበሩ በየዓመቱ የተሻለ የትርፍ ክፍፍል እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ከትርፍ ክፍፍሉ በተጨማሪ ማህበሩ በአካባቢው በሚያከናወነው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
እንደ አርሶ አደር ምርጋ ገለጻ፣ ዘንድሮም እስካሁን ድረስ ከ2 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ጥራቱን የጠበቀ እሸት ቡና ለማህበሩ አቅርበዋል።
ከቡና ልማት ሥራቸው በየዓመቱ የሚያገኙት የትርፍ ክፍፍል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገው መምጣቱንም ተናግረዋል።
የፉራና አካባቢው የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ደቀማ ዳቤሳ በበኩላቸው፣ ማህበሩ ከአባል አርሶ አደሮች የሚሰበስበውን ቡና ለዩኒየን እንደሚያስረክብ ተናግረዋል፡፡
ከቡና ሽያጭ ሕብረት ሥራ ማህበሩ በዓመት እስከ 30 ሚሊዮን ብር ትርፍ እንደሚያገኝና 70 ከመቶውን ለአባላቱ እንደሚያከፋፍልም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በስድስት ቀበሌዎች የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት አባላቱንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
ማህበሩ በዘንድሮው የምርት ወቅት ከ2 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ቡና ለመሰብሰብ አቅዶ እስካሁን 500ሺህ ኪሎ ግራም እሸት ቡና በጥራት የማዘጋጀቱን ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሸበዲኖ ወረዳ ህብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሃያሞ ሰሞ በወረዳው 12ሺህ 358 አባላትን ያቀፉ አራት የአርሶ አደሮች ሕብረት ሥራ ማህበራት መኖራቸውን ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት 97 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘታቸውን ለአብነት የጠቀሱት ሃላፊው አባላቱ ከህብረት ሥራ ማህበሩ በተጨማሪ ከዩኒዮንም የትርፍ ክፍፍል እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡
በዚህም አርሶ አደሩ ከሚያመርተው ቡና ከፍ ያለ ዋጋ እንዲያገኝ ከማድረጉ ባለፈ በአካባቢው በሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በወረዳው በ25 ኢንዱስትሪዎችና ቡና ላኪ አርሶ አደሮች አማካይነት እሸት ቡና የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሸበዲኖ ወረዳ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ካርታ ፍስሃ ናቸው፡፡
በወረዳው ከ12 ሚሊዮን 600 ኪሎ ግራም በላይ እሸት ቡና ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ድረስ 50 ከመቶ በላይ የሚሆነው ምርት ተሰብስቧል ብለዋል፡
በቡና ልማቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮች፣ ማህበራት፣ አክስዮኖችና ባለሃብቶች በቡና ጥራት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉንም ሃላፊው ገልጸዋል።