የመደመር መንግሥት በከተሞች ልማት ያከናወናቸው ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አረጋግጠዋል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት በከተሞች ልማት ያከናወናቸው ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አረጋግጠዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦መደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት በከተሞች ልማት፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና በመኖሪያ ቤት ግንባታ ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጣቸውን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን ገለጹ።
የ2026 የዓለም የከተሞች ቀን «ከተማን ማደስ በኢትዮጵያ ከተሞች፤ ለሁሉም የሚተርፍ በቂ መኖሪያ ቤት» በሚል መሪ ሀሳብ በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በዩኤን ሀቢታት (UN-Habitat) በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ትኩረቱንም በከተሞች እድገት፣ በመኖሪያ ቤት አቅርቦት እና በከተማ ማደስ ስራዎች ዙሪያ አድርጓል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተሞች ልማትና በመኖሪያ ቤት ግንባታ ያከናወናቸው ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው።
ከተሞች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የፈጠራ ሥራዎች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማህበራዊ ትስስር ማዕከላት እንዲሆኑ በትኩረት መሰራቱን ገልፀዋል።
በተለይም በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል የቤት ልማት ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው፤ በመደመር መንግሥት እውን እየሆነ ያለው የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለዚህ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከናወኑት የኮሪደር ልማቶች እና የከተማ ማደስ ስራዎች ከተሞቻችን ንጹህ፣ ለኑሮ ምቹ እና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሰጡ እንዲሆኑ አድርገዋል ብለዋል።
ይህም ከተሞቹ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ሳቢነት አቅም እንዲኖራቸው ማስቻሉን የገለጹት ሚኒስትሩ እነዚህና መሰል ስራዎች በዘርፉ እመርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ እድል ፈጥረዋል ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም፣ከልማት አጋሮች፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን አጋርነት በማስፋት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የከተማ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠልም ለዜጎቿ ምቹ የሆነችና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አፅንኦት ሰጥተዋል።