የመደመር መንግሥት ለሀገር ውስጥ ምርቶች ቀልጣፋ እና ውጤታማ የውጭ ገበያ እድሎችን እያሰፋ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ለሀገር ውስጥ ምርቶች ቀልጣፋ እና ውጤታማ የውጭ ገበያ እድሎችን እያሰፋ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት የንግዱ ማህበረሰብ ምርቱን ወደተለያዩ ሀገራት በቀላሉና በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲልክ የሚያስችሉ ውጤታማ የውጭ ገበያ እድሎችን እያሰፋ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ ገለጹ።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ እንደገለጹት፣ መንግሥት ለንግድ ዘርፉ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በርካታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለንግዱ ማህበረሰብ ከቀረጥ ነፃ ዕቃዎችን የማስገባት እና የውጭ ምንዛሬ ችግሮችን ለመቅረፍ ከባንኮች ጋር በማስተሳሰር ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በመንግሥት በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ለውጭ ገበያ በቀላሉና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲቀርቡ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ከእነዚህም መካከል የንግድ ለንግድ (B2B) ትስስር መድረኮችን በመፍጠር ከፍተኛ የገበያ ትስስር ለማምጣት እየተሰራ ያለው ስራ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
በዚህም በርካታ የዓለማችን ሀገራት በኢትዮጵያ በንግድ ዘርፍ ለመሰማራት፣ ምርቶችን ለመግዛትና ወደ ውጭ ለመላክ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
ይህም አሰራር ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብና ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ከውጭ ገዢዎች ጋር የሚያገናኙ የንግድ ለንግድ ትስስሮችን በመፍጠር የውጭ ገበያ እድሎችን እያስፋፋ ይገኛልም ብለዋል።
በዚህም መሠረት በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደ አዘርባጃን፣ ቱርክ፣ ቻይና እና ከበርካታ የአውሮፓ ሀገራት በጠቅላላው ከ20 እስከ 25 ከሚደርሱ ሀገራት ጋር የመግባቢያ ሰነዶችን መፈራረሙን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በቡና፣ በግብርና፣ በፋርማሲዩቲካልስ እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ የውጭ ኢንቨስተሮችና ነጋዴዎች እንዲሳተፉ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
እነዚህ የትስስር መድረኮች ለነጋዴው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ሲሉም ገልጸዋል።