በአማራ ክልል በአየር ንብረት መዛባት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ በበጋ መስኖ ለማካካስ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በአየር ንብረት መዛባት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ በበጋ መስኖ ለማካካስ ትኩረት ተደርጓል
ባህርዳር፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ በበጋ መስኖ ለማካካስ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለፁ።
በገጠር ክላስተር ስር የሚገኙ ተቋማት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በባህር ዳር አካሄደዋል።
የክላስተሩ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፤ በክልሉ በአየር ንብረት መዛባት ሊያጋጥም የሚችለውን ምርት መቀነስ በበጋ መስኖ ለማካካስ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።
በዚህም የአየር ንብረት መዛባቱ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀልበስ ቅንጅታዊ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
የዘርፉ ቢሮዎች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የጋራ ዕቅድ በማውጣትና ውጤታማ የአፈጻጸም ሥርዓት በመዘርጋት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተፈጥሮ አደጋው ሊቀንስ የሚችለውን ምርት ለማካካስ አርሶ አደሩ በማሳው ዳርና መሃል ላይ ውሃ እንዲያሰባስብ የተደረገው ጥረት መልካም ውጤት ታይቶበታል ብለዋል።
በተጨማሪም በመኸሩ ሊታጣ የሚችለውን ምርት በበጋ መስኖ ለማካካስ አርሶ አደሩ ፈጥኖ ወደ መስኖ ልማት እንዲገባ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
በሩብ ዓመቱ የተገኙ መልካም ውጤቶችን የቀጣይ ስኬቶች መስፈንጠሪያና ችግሮችን ደግሞ መማሪያ በማድረግ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የክላስተሩ ተቋማት መረባረብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መስፍን አበጀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በምርት ዘመኑ ከለማው ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።
ቢሮው ወደ ዘመናዊ የግብርና አሠራር ለመሸጋገር ግብ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህም በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በኤልኒኖ ሊታጣ የሚችለውን ምርት በመስኖ ለማካካስ በበጋ ወቅት ከ734 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በነባርና አዲስ መስኖ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 26 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።
በገጠር ካዳስተር የ2ኛ ደረጃ የመሬት ማረጋገጫ ያገኙ አርሶ አደሮች በሩብ ዓመቱ ብቻ የመሬታቸውን ካርታ በማስያዝ የአንድ ቢሊዮን ብር ብድር ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ደግሞ የክልሉ መሬት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰይፉ ሰኢድ ናቸው።
ይህም አርሶ አደሩ ያገኘውን ብድር ተጠቅሞ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች በመሰማራትና የመሬቱን ለምነት በማሳደግ ምርታማነቱን ለማላቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ የክላስተሩ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮችና ሌሎች ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።