ቀጥታ፡

ክልሉን ለኢንዱስትሪ ተመራጭ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ውጤት አስገኝተዋል 

ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ የአማራ ክልልን በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ውጤት ማስገኘታቸውን  የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው አዲስ ያለማውን "የኢንቨስትመንት ማኔጅመንት ሲስተም (IMS)" ወደ ተሟላ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል የፈጻሚዎች ሥልጠና ዛሬ አስጀምሯል።


 

የቢሮው ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በሥልጠናው ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት፤ ክልሉን በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ውጤት አስገኝተዋል።

በቀጣይም ግልጽ፣ ፍትሐዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለባለሀብቱ በመስጠት ክልሉን የኢንቨስትመንት ቀጠና ለማድረግ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም ደንበኞች ለሚያቀርቡት የኢንቨስትመንት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና የሚስተዋሉ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ተግባሩን ወደ መሬት ለማውረድም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር ከ17 በላይ አበይት አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል "ዘመናዊ የኢንቨስትመንት ማኔጅመንት ሲስተም" ማልማት ተችሏል ብለዋል።

የአሁኑ ሥልጠናም በሙከራ ትግበራ ላይ የነበረውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር ወደ ተሟላ ትግበራ በማስገባት ፈጣንና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ለማስፈን ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

የተቋሙ የቡድን መሪዎችና ባለሙያዎችም በሥልጠናው የሚያገኙትን የሲስተሙ አተገባበር ዕውቀት፣ አሠራርና ልምድ በመጠቀም ዘርፉን ለማሳደግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ደንበኞችም ቢሮው ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ መሸጋገሩን በመገንዘብ ባሉበት ሆነው የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ከዘመናዊ አሠራሩ ጋር ራሳቸውን እንዲያላምዱ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው የሥልጠና መድረክ የቢሮው አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም