ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ልማት በፍትሐዊና ምክንያታዊ የትብብር መንፈስ ላይ የተመሰረተ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶች የውሃና ኢነርጂ ልማት በፍትሐዊና ምክንያታዊ የትብብር መንፈስ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት «ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶች ማሳደግ» በሚል መሪ ሃሳብ መካሄድ ጀምሯል።

በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በይፋ በተከፈተው መርሃ ግብር ላይ የሀገራት አምባሳደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በተወካያቸው በኩል እንደገለጹት፤ የውሃና ኢነርጂ ልማት የአካባቢ ጥበቃን በማጎልበት የሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት መሠረቶች ናቸው ብለዋል።

ሁለቱ መሠረታዊ ሀብቶችም የግብርና ምርታማነትን በማሳለጥ ለምግብ ዋስትና፣ የሕዝብ ጤና፣ ኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለአካባቢ ዘላቂ ደኅንነት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያን የውሃና ታዳሽ ኢነርጂ አቅም በሳይንሳዊ ጥናትና በተረጋገጠ የፖሊሲ መረጃ በማስደገፍ ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም የኃይል አቅርቦት፣ የውሃና ንጽህና አጠባበቅ ሥርዓት፣ የመስኖ ልማትና የውሃ አጠቃቀም፣ የገጸና ከርሰ ምድር የውሃ ሀብቶችን ልማት ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያን የውሃና ኢነርጂ መሠረተ ልማቶችን በማስፋት ዜጎች የሚፈልጉትን የአገልግሎት አቅርቦት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን የውሃና ኢነርጂ ልማት ለማፋጠንም የመንግሥት፣ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍና በልማት አጋሮች መካከል የሚደረገውን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችንም ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን በማረጋገጥ በትብብርና በመተማመን ላይ በተመሠረተ አካሄድ የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት እየተጋች መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ልማት በትብብር፣ በፍትሐዊና ምክንያታዊ የሀብት አጠቃቀም እንዲሁም የጋራ ብልጽግናን በሚያረጋግጥ አጋርነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።

መድረኩም በሳይንሳዊ መረጃ የተደገፉ ፖሊሲዎችንና ትብብርን በማጠናከር ለዘላቂ የውሃና ኢነርጂ ዋስትና የሚያግዙ ሀሳቦችን፣ ልምዶችንና መፍትሔዎችን ለመለዋወጥ የሚያስችል መሆኑን ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም