ቀጥታ፡

ሠራዊቱ የሃገር ዳር ድንበርና ሰላምን የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ  ነው -ሜጄር ጀነራል ፍቃዱ ፀጋዬ

ሐረር፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ ሠራዊቱ የሀገር ዳር ድንበርና ሰላምን የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ የዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጀነራል ፍቃዱ ፀጋዬ ተናገሩ።

119ኛው የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት ቀን "የድል ሠራዊት"በሚል መሪ ሀሳብ በሐረር ከተማ በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።


 

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጀነራል ፍቃዱ ፀጋዬ እንደገለጹት፤ ሠራዊቱ ሰላምና የሀገር ዳር ድንበርን የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ነው።

ዕዙ በተለያዩ ጊዜያት የተሰጠውን ተልዕኮና ግዳጅ በላቀ ብቃት በመወጣት ስኬታማ አፈፃፀም እያስመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።

የእዙ አባላትም የሀገርን ሰላም የሚያውኩ ፀረ ሰላም ሃይሎችን ተከታትሎ በማጥፋት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ደሕንነት የማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን በብቃትና በጀግንነት እየተወጡ መሆኑንም አመልክተዋል።

በቀጣይም የሀገርን ዳር ድንበርና የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በሚከናወኑ ተግባራት የእዙ አባላት ተልዕኳቸውን በብቃት ይወጣሉ ብለዋል።


 

119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ትላንት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር  የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ ዕድሜ ጠገብ ተቋማት ከገነቡ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ካሉ ዕድሜ ጠገብ ተቋማት መካከልም 119 ዓመት ያስቆጠረው የሀገር መከላከያ ቀዳሚና አንጋፋ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሠራዊቱ ዛሬም ሀገር ለማፍረስ የተነሱ ባንዳዎችን በጀግንነት በመዋጋት የሀገር መከታና ምሶሶ መሆኑን መናገራቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም