ቀጥታ፡

የሀገር ሉዓላዊነት እና የብሔራዊ ጥቅም አስተማማኝ መከታ

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት፦የሀገር ሉዓላዊነት እና የብሔራዊ ጥቅም አስተማማኝ መከታ 

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በአስተማማኝ ሁኔታ የማስከበር ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት የተጣለበት የሉዓላዊነታችን ዓምድ ነው። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ ስትራቴጂካዊ የጂኦ-ፖለቲካ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን፣ የሰራዊቱ ጥንካሬ እና ዝግጁነት ለሀገር ውስጥ ሰላም ብቻ ሳይሆን ለመላው ቀጣናዊ መረጋጋት የጸና ዋስትና ነው። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከቀድሞው ባህላዊ የውጊያ ልምድ እና ታሪካዊ የጀግንነት መሠረት ተነስቶ፣ ዛሬ ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ በከፍተኛ ሳይንሳዊ እውቀት እና ፕሮፌሽናሊዝም የተገነባ የጦር ኃይል ሆኖ መውጣቱ በጉልህ የሚታይ ስትራቴጂካዊ ሽግግር ነው።

የሰራዊቱ መዋቅራዊ እና ሞራላዊ መሰረት ከብዙ ዘመናት የሀገር ፍቅር ወግ ጋር የተሳሰረ ነው። የሰራዊቱ ዋና የሞራል ምንጭ ሀገርን ከውጭ ወረራ የመከላከል እና ታሪካዊ ድሎችን የመቀዳጀት የዘመናት ባህል ነው። የ1888 ዓ.ም. የዓድዋ ድል ሙሉ በሙሉ በህዝባዊ ክንድ እና በሀገራዊ ፍቅር ላይ የተመሰረተ የነጻነት ተምሳሌት በመሆን ለዘመናዊው ሰራዊት የጽናት እና የማንነት መሠረት ሆኖ ያገለግላል። በተመሳሳይ መልኩ የ1970 ዓ.ም. የካራማራ ድል የሀገርን ሉዓላዊነት እና ወሰን ለማስከበር የተከፈለ የላቀ መስዋዕትነት እና ወታደራዊ ስትራቴጂካዊ የበላይነት የታየበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

የኢትዮጵያ ሰራዊት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥነ-ምግባሩና በውጊያ ብቃቱ የተመሰገነ ተቋም ነው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በ1950ዎቹ በኮሪያ እና በኮንጎ የተከናወኑት የመጀመሪያዎቹ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች፣ በኋላም በሩዋንዳ እና በቡሩንዲ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ሰላም የመመለስ ስራዎች የሰራዊቱን ዓለም አቀፍ ክብር ከፍ አድርገውታል። በቅርብ ጊዜያት ደግሞ በሱዳን (አብዬ) እና በሶማሊያ ቀጣናውን የሚያናውጠውን የሽብርተኝነት ስጋት በመመከት የሰላም አየር እንዲነፍስ በማድረግ ረገድ ሰራዊቱ የላቀ አህጉራዊ አመኔታን አትርፏል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን የጦርነት እና የደህንነት ስጋቶች ቅርፃቸውን በመቀየራቸው፣ ባህላዊ የሰው ኃይል ውጊያ ብቻውን በቂ አለመሆኑን በመረዳት ሰራዊቱ ሰፊ የቴክኖሎጂ እና የትጥቅ ማሻሻያዎችን አድርጓል። በአየር ኃይል ዘርፍ የዘመኑን ስትራቴጂካዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በስፋት በመታጠቅ የአየር ላይ ቅኝት፣ መረጃ የመሰብሰብ እና ተልዕኮ የመፈጸም ብቃቱን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል።

በሌላ በኩል የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የመከላከያ መረቦችን እና ሀገራዊ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ከጥቃት የመጠበቅ አቅም ገንብቷል። የምድር ኃይሉም ዘመናዊ ታንኮች፣ የታጠቁ የሰው ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች፣ የረጅም ርቀት የሚምዘገዘጉ መድፎች እና የባለብዙ ሮኬት ማስወንጨፊያ ስርዓቶችን በመታጠቅ የመከላከል እና የማድረግ አቅሙን አጠናክሯል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሙሉ በሙሉ በውጭ ሀገራት የትጥቅ ግዢ ላይ ጥገኛ ከመሆን ለመውጣት በሀገር ውስጥ የሚገኙ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማሳደግ ጥይቶች፣ ቀላል እና ከባድ የጦር መሳሪያዎች፣ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች እና የመገናኛ መሳሪያዎች በሀገር ውስጥ የማምረት እና የመጠገን ስራ እየተከናወነ ይገኛል። በተለይም የሰራዊቱ ወታደራዊ አልባሳት ጭምር በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ መደረጉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን የማዳን ትልቅ እርምጃ ሆኗል።

ማንኛውም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤታማ የሚሆነው በሰለጠነ እና በተገነባ የሰው ኃይል ሲመራ በመሆኑ፣ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሰራዊቱን አባላት በኢንጂነሪንግ፣ በህክምና፣ በሳይበር ቴክኖሎጂ እና በኮምፒዩተር ሳይንስ በዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ በማሰልጠን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የጦር አካዳሚዎች እና የሰራተኞች ኮሌጅ (Staff College) ደግሞ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮችን በስትራቴጂካዊ ወታደራዊ መሪነት፣ በዘመናዊ የውጊያ ስልት እና በጂኦ-ፖለቲካዊ ትንተና እያሰለጠኑ ያወጣሉ። ይህም ሰራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ እና የብሔር ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ፣ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለህዝብ ደህንነት እና ለህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ታማኝ የሆነ ፕሮፌሽናል ኃይል ሆኖ እንዲደራጅ አስችሎታል።

ለወደፊቱ ስትራቴጂካዊ ዝግጁነቱን ለማረጋገጥ ሰራዊቱ በርካታ ተፎካካሪ ሁኔታዎችን በመለየት እየሰራ ይገኛል። የዘመናዊ ትጥቅ እና ቴክኖሎጂ ውድነትን እና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቋቋም ሀገር በቀል የምርምር እና የማምረት አቅምን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል። የባህር ኃይልን እንደገና የማደራጀት እና ቀጣናዊ ትብብር የመፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን  ሰው ሰራሽ አስተውሎትን መሰረት ያደረጉ የውጊያ ስርዓቶችን እና የመረጃ ትንተና ቴክኖሎጂዎችን የማዋሃድ የቴክኖሎጂ አቅጣጫም ተይዟል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የጀግንነትና የውጤታማ ግዳጅ አፈጻጸም ህያው ማሳያ ነው። ለዚህ ደግሞ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና ዘመኑን የዋጁ አሰራሮችን መከተሉ ግዳጆችን በብቃትና በውጤታማነት እንዲፈጽም መሠረት ሆነውታል። ሰራዊቱ ለግዳጅ በሚሰማራበት ሀገራዊም ሆነ አህጉራዊ ቀጣናዎች ደህንነትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ከህዝብ ጋር በጋራ በመሆን ማህበራዊ ኃላፊነቱን በስኬታማነት በመወጣት የህዝብ ኩራት ሆኗል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ጉዞ የታሪካዊ ጀግንነት፣ የጽናት እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውህደት ድንቅ ውጤት ነው። ሰራዊቱ ከዓድዋ እስከ ካራማራ፣ እንዲሁም እስከ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያስመዘገበውን ታሪካዊ የጀግንነት ስም አሁን ካለው የ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂ እድገት ጋር በማቀናጀት ጠንካራ ተቋም ገንብቷል። ይህ የጀግንነት እና የዘመናዊ አቅም ቅይጥ ሰራዊቱ በምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና የሀገር ሉዓላዊነት አስተማማኝ መከታ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም