ቀጥታ፡

ከውጭ ጥገኝነት ወደ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት፡ የተኪ ምርት ስትራቴጂካዊ ሚና

የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገሪቱን የንግድ ሚዛን መዛባት በዘላቂነት ለማስተካከል መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ እያካሄደ ይገኛል።

የተኪ ምርት ጅማሮ በዋናነት ያተኮረው በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ወጪን በማስቀረት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ላይ ነው።

ቀደም ሲል በተበታተነና ዝቅተኛ በሆነ መልኩ ሲካሄድ የነበረው የማምረት ተግባር ወደ ተቋማዊ አሰራር የቀየረ ይፋዊ ብሔራዊ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ጸድቆ ወደ ስራ ገብቷል።

ስትራቴጂው ለቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሚቆይ ፍኖተ ካርታ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ለትግበራው መፋጠን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ እንደ ትልቅ ሞተር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።


 

ሀገራዊ ንቅናቄው በ2016 ዓ.ም ተግባራዊ መሆን ለጀመረው ብሔራዊ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

የስትራቴጂው መውጣት እና ወደ ተግባር መግባት በሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማስገኘት ጀምሯል።

የሀገር ውስጥ አምራቾች በገበያ ላይ ያላቸው የምርት ድርሻ ወደ 45 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ የፋብሪካዎች አማካይ የማምረት አቅምም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ብሏል።

ይህ መነቃቃት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረ ከመሆኑም በላይ የፋብሪካዎችን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ከሀገር ውስጥ የግብርና እና የማዕድን ምርቶች ጋር በማስተሳሰር የአቅርቦት ሰንሰለቱን አጠናክሮታል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የምግብ እና የማዳበሪያ አቅርቦት መስተጓጎል በመጥቀስ፣ የሀገር ውስጥ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ኢትዮጵያን ከከፋ የምግብ እጥረት እንደታደጋት መግለጻቸው ይታወቃል።

ተኪ ምርት ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነት እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ይወጣባቸው የነበሩ የድንጋይ ከሰል እና የችፑድ ምርቶች አሁን ላይ በሀገር ውስጥ በስፋት እየተመረቱ መሆናቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም