የሀገርን ዳር ድንበር እና የህዝብን ሰላም እያስጠበቀ የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የማንደራደርበት ቀይ መስመራችን ነው - የመከላከያ ሰራዊት የክብር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ዳር ድንበር እና የህዝብን ሰላም እያስጠበቀ የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የማንደራደርበት ቀይ መስመራችን ነው - የመከላከያ ሰራዊት የክብር አባላት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦ የሀገርን ዳር ድንበር እና የህዝብን ሰላም እያስጠበቀ የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የማንደራደርበት ቀይ መስመራችን ነው ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት የክብር አባላት ገለጹ።
በ119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ለሠራዊቱ በግላቸው በማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ የፈጠሩ እና በተለያዩ ሚድያዎችም ከሀገር ውጭም ጭምር ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዜጎች የክብር የመከላከያ ሠራዊት አባልነት እውቅና ተሰጥቷል።
የክብር አባላቱ ከኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እጅ የክብር የመከላከያ ሠራዊት አባልነት እውቅናቸውን ተቀብለዋል።
እውቅና ከተሰጣቸው መካከል የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ወጣቶች ህብረት ፕሬዝደንት ቢኒያም ጌታቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የማንደራደርበት ቀይ መስመር ነው ብሏል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ከየትኛውም ፓርቲ፣ግለሰብ እና ድርጅት ውስጥ መክተት እንደማይገባ ገልጿል።
መከላከያ የሀገርን ዳር ድንበር እና ሰላም የሚያስጠብቅ ራሱን የቻለ ተቋም መሆኑን ተናግሯል።
ሁሉም ሰራዊቱ ለሀገር እየከፈለ ያለውን ዋጋ በመገንዘብ ሊወደው እና ሊያከብረው እንደሚገባ አስገንዝቧል።
ሌላኛው የመከላከያ የክብር አባልነት እውቅና ያገኘው አፈወርቅ በደዊ በበኩሉ ኢትዮጵያውያን ወታደራዊ ስነ ልቦና እና ዲስፐሊን ያላቸው ህዝቦች ናቸው ብሏል።
የሰራዊቱ አባልነት በየትኛውም መንገድ እና አይነት እንዲሁም በየትኛውም ሁኔታ ማንም የማይጸጸትበት ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ጠቁሟል።
ሌሎች ዋጋ ይከፍላሉ ብሎ መጠበቅ እንደማይገባ ገልጾ ሁሉም ኢትዮጵያ የተፈራች፣የተከበረች እና የታፈረች ሀገር እንድትሆን ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝቧል።
119ኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሀሳብ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ በዛሬው እለት ተከብሯል።
በመርሀግብሩ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣የመከላከያ ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ የቀድሞ የሠራዊቱ አመራሮች፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎቾ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የሠራዊት ቀን የመከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ መልኩ ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም የተመሰረተበትን ታሪክ በማሰብ ይከበራል።
ቀኑ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ሚኒስትር የሰየመችበትን ቀን በማስታወስ ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ይዘከሩበታል።
ዓላማውም የሠራዊቱን ጀግንነት፣ ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ሚና እና ታላቅ አኩሪ ታሪክ ለትውልድ በቅብብሎሽ ማስተላለፍ ነው።