በቤንች ሸኮ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራት ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
በቤንች ሸኮ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራት ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ተሳትፏችንን እናጠናክራለን
ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ):- በቤንች ሸኮ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራት ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ተሳትፏችንን እናጠናክራለን ሲሉ የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ከፍተኛ አመራሮች ጋር በልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በሚዛን አማን ከተማ ተወያይተዋል።
በወቅቱም ነዋሪዎቹ፤ በቤንች ሸኮ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራት ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ተሳትፏችንን እናጠናክራለን ብለዋል ።
ከውይይት መድረኩ ተሳታፊ ነዋሪዎች መካከል አቶ አስቻለው ወይታና አቶ ደምሴ ባይናንስ፣ መንግሥት ባከናወናቸው ተግባራት የቆዩ የሕዝብ መሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ልማት በመንግሥት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ተሳትፏቸውን በማጠናከር ለአካባቢያቸው ለውጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የሚዛን አማን ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ሻንቆ ጋኪናንስ፣ የገጠርና የከተማ ኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችና ሌሎችም ኢኒሼቲቮች የአካባቢያችንን ገጽታ የቀየሩ ውጤታማ ተግባራት ናቸው ብለዋል።
በተለይ፣ የፍትሐዊ የልማት ተደራሽነት ማረጋገጫ የሆኑት የደንቢ ኢኮ ሎጅና የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ በአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃትን የፈጠሩ ፕሮጀክቶች ስለመሆናቸው አንስተዋል።
የምናመርታቸውን የግብርና ምርቶች ወደ ገበያ ለማውጣት የመንገድ መሠረተ ልማት ተግዳሮት እየሆነ በመምጣቱ፣ በቀጣይ ትኩረት እንዲሰጠው የጠየቁት ደግሞ የሸኮ ወረዳ ነዋሪ አቶ ንጉሤ ሴዚ ናቸው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ የመደመር መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በቅርበት እየተወያየ የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት ይሠራል ብለዋል።
በክልሉ የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄ ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቅሰው፣ በፌዴራል መንግሥት የሚሠሩ ግንባታዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በቅንጅት በአጭር ጊዜ እንዲፈቱ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ቀበሌን ከቀበሌና ከወረዳ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች በኅብረተሰብ ተሳትፎ ግንባታቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዝርጋታ፣ የኔትወርክና ሌሎች የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።
በክልሉ መንግሥት የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተው፣ የተያዙ የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።