ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሞዴሎችን በማልማት የኢትዮጵያን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሚናችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሞዴሎችን በማልማት የኢትዮጵያን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሚናችንን እንወጣለን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦የሀገር ውስጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሞዴሎችን በማልማት የኢትዮጵያን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የራሳችንን ሚና እንወጣለን ሲሉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የልዩ ተሰጥኦ ትምህርት ማዕከል ተማሪዎች ገለፁ።
ማዕከሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በቡራዩ ከተማ በ4 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውና እስከ አንድ ሺህ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለው ዘመናዊው የልዩ ተሰጥኦ ማዕከል ነው።
ማዕከሉ ከፍተኛ የማሰብ፣ የፈጠራ እና ትኩረት የማድረግ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በማሰባሰብ ሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ ያለመ ሰፊ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል።
በዚህም ማዕከሉ በቅርቡ የመጀመሪያ ባች የሆኑ ሁለት መቶ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰልጣኞች አስመርቋል።
በዚሁ ልዩ የስልጠና ፕሮግራም አልፈው ከተመረቁትና ውጤታማ ስራዎችን በማቅረብ ላይ የሚገኙት ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት በአገኙት እውቀት ኢትዮጵያ በዘርፉ የጀመረቻቸው ስራዎች ውጤታማነት የበኩላቸው ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ርብቃ በጋሻው ከኮሌጅ ህይወቷ ጀምሮ የሀገርን የዲጂታል ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ ገለልተኛ የዳታ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሲስተም በራስ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ስታስብ መቆየቷን አስታውሳለች።
በዚህም ከማዕከሉ ባገኘችው በተግባር የተደገፈ ስልጠና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ከእውቀትና አመራር ጋር በማጣመር የበኩሏን ስራ ለመስራት መዘጋጀቷን ተናግራለች።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በተሻለ አበበ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ሲሆን፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በኩል በሚሰጠው የሳይኮሜትሪክ ምዘና አልፎ ወደ ማዕከሉ መቀላቀሉ ተናግሯል።
በቆይታውም በሳይበር ደህንነትና መልቲሚዲያ ላይ ትኩረት አድርጎ የሰራ ሲሆን፣ ወደፊት በኤአይ ኢንጂነሪንግ (AI Engineering) ሀገሩን ለማገልገል መዘጋጀቱን በመግለጽ ወጣቶች ያሉትን የኢንተርኔት እና የሰመር ካምፕ ዕድሎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) ከሀገሯ የአቪዬሽን ዘርፍ ጋር ለማስተሳሰር በመስራት ላይ እንደምትገኝ የተናገረችው ደግሞ በኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት የኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ማክዳ ወርቅነህ ናት።
በአሁኑ ወቅት የአውሮፕላኖችን ጥገና ወጪ ለመቀነስ እና ብልሽት ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መተንበይ የሚያስችል ፕሮጀክት ማዘጋጀቷን ገልጻለች።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር መሳይ ሀይለማርያም በበኩላቸው ማእከሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች አቅም በማውጣት ረገድ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም ታዳጊዎች የፈጠራ ክህሎትና ልዩ ተሰጧቸውን በማበልጸግ ችግር ፈቺ ውጤቶችን የሚያፈልቁበት ወሳኝ ዕድል እየፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ወጣቶች የሚያፈልቋቸውን የፈጠራ ስራዎች ከሀገር ውስጥና ከውጭ አጋሮች እንዲሁም ከግል ባለሃብቶች ጋር በማስተሳሰር ምቹ የስታርት አፕ ምህዳር ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የእነዚህን ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች መብትና ደህንነት በጠበቀ መልኩ ተሰጥዋአቸውን በመለየት እና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት አወንታዊ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።