የወንዝ ዳርቻ ልማት የመደመር መንግሥት የተሟላ የልማት አቅም እንዳለው በተግባር ያሳየ ነው-አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የወንዝ ዳርቻ ልማት የመደመር መንግሥት የተሟላ የልማት አቅም እንዳለው በተግባር ያሳየ ነው-አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦የወንዝ ዳርቻ ልማት የመደመር መንግሥት የተሟላ የልማት አቅም እንዳለው በተግባር ያሳየ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀጨኔ፣ አምባሳደር፣ ጊዮን-ኢሬቻ፣ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የ351 ሄክታር አጠቃላይ ስፋት እና የ10 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለውን የኮሪደር ልማት ዘመናዊ፣ አረንጓዴ እና ሁሉንም አካታች የሆነች አዲስ አበባን የመገንባት ራዕያችንን እውን የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የእግረኛ መንገዶችን፣ የብስክሌት መንገዶችን እና የተቀናጁ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን ያካተተ በመሆኑ፣ ይህ ልማት ይበልጥ ተደራሽ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ የከተማ ከባቢን ይፈጥራል ሲሉም ገልጸዋል።
የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ፕላዛዎችና አምፊ ቲያትሮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ እንዲሁም የውሃ ትርዒት ማሳያዎች ለመዝናኛና ማህበራዊ ግንኙነት አዳዲስ ዕድሎችን ያበረክታሉም ብለዋል።
የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እና ከ100 በላይ መኪኖችን በአንድ ጊዜ መሙላት የሚያስችሉ ስምንት የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ማዕከላት የዘመናዊ መሠረተ ልማቱን አቅም ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማቱን አስመልክቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ በሰጡት ማብራሪያ የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራው ዓለም አቀፍ የግንባታ ደረጃን በጠበቀ ጥራት የተሰራ ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት ባለፉት አመታት ለከተሞች እድገት በሰጠው ትኩረት ከተሞች የኢኮኖሚ ማግኛ ምንጭ በመሆን ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ እድል ፈጥሯል።
የቀጨኔ፣አምባሳደር፣ጊዮን-ኢሬቻ፣ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋን ሌላ ገጽታ አጉልቶ ያሳየ ትልቅ የልማት ስራ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም አረንጓዴ፣ንጹህና ለኑሮ ተስማሚ ተደርጎ መገንባቱ የከተማዋን ተወዳዳሪነት ከፍ አድርጎታል ነው ያሉት።
በዋናነት በልማቱ የተካተቱ ተጨማሪ መሰረተ ልማቶች ለዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠረ ለትውልድ ግንባታ ስራ አሻራ የሚጥሉ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የወንዝ ዳር ልማቱ አካባቢን ከማስዋብ ባሻገር የከተማዋን የውሃ ሃብት ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ እድል የፈጠረ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
እንዲሁም አዳዲስ የመኪናና የእግረኛ አማራጭ መንገዶች የልማቱ አካል ተደርገው መገንባታቸውን የገለጹት አፈ ጉባኤው የመደመር መንግስት የተሟላ የልማት አቅም እንዳለው በተግባር ያሳየ ነው።
የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራው በዙሪያው ያለውን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ መገንባቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች አዲስ የህይወት ምዕራፍ የሚከፍት ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ይህም ለከተማዋ ነዋሪዎች ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን ይዞ ከመምጣት ባሻገር ተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲጎለብት በማድረግ ለእርስ በእርስ ትስስር መጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
የልማት ስራው ለሌሎች የሀገራችን ከተሞች ምሳሌ የሚሆንና በልማት ስራ የሚደረግ የጋራ ጥረት የሚያስገኘውን ውጤት የሚያመላክት መሆኑንም አንስተዋል።
በሁሉም አካባቢዎች የተከናወኑ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች ለሁለንተናዊ ማህበራዊ የኑሮ ጥራት መሻሻል፣ለአረንጓዴ ልማት፣ለኢኮኖሚያዊ እድገት፣ለአካባቢ ውበትና ጽዳት ትልቅ ለውጥ ማምጣት ችሏል ነው ያሉት።