ቀጥታ፡

ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ለመስጠት እየተጋች ያለች ሀገር-ኢትዮጵያ

በየፀዳወርቅ ታደለ (ኢዜአ)

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትን በመመስረት አህጉሪቱ በሁሉም መስክ ጽኑ ትስስር እንዲኖራት የመሪነት ሚናዋን ተጫውታለች። በዚህም አፍሪካ በቅኝ ግዛት ማዕበል ስትናወጥ  በታላቅ ጀግንነት በመጽናት ለሌሎች አርአያ መሆን የቻለች ታላቅ ሀገር ነች። ይህ የነጻነት ዋጋ በታሪክ ደም ታትሞ ለአህጉራችን የድል አርማ ሆናለች።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንገብጋቢ ጉዳዮች መፍትሔ የሚፈለግባት፣ የአህጉሪቱ አንድነት የሚመከርባት የሰላምና የዲፕሎማሲ ጮራ ናት።አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ኢትዮጵያ  የእኛም ሀገር ናት ብለው ያለ ማመንታት በኩራትና በፍቅር በእቅፏ የሚገኙ የሁልጊዜም መኖሪያቸው ነች።

የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የዓለም የዲፕሎማቲክ ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የአህጉሪቱ መሪዎች የሚሰበሰቡባት፣ የአፍሪካ አንገብጋቢ ጉዳዮች የሚመከሩባት እና የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚወሰንባት የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት።

ኢትዮጵያ ከመደበኛው የፖለቲካ መድረክ በተለዬ መልኩ እና  የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማዕከል በማድረግ የሚዘጋጀውን የጣና ፎረም ለ15 ዓመታት በስኬት እያስተናገደች መጥታለች።

የዘንድሮው 12ኛው የጣና ፎረም "አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የቀጣናዊ ፖለቲካዊ ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ ጥቅምት 13 ቀን በባህርዳር ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህ መድረክም  የአህጉራችን የሰላም፣ የጸጥታና የደህንነት ጉዳዮች በአንድነት የሚመከርበት ሌላኛው የኩራት ማማችን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም መፍትሔ በማፍለቅ፣የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ የዘንድሮው የጣና ፎረም የትኩረት አጀንዳ መሆኑን በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

አፍሪካ የሚከሰቱ ሁሉንም አደጋዎች መቆጣጠር እንደማይቻል ሲገልጹ የዜጎችን አይበገሬነት ማጠናከር ግን ከእኛ ይጠበቃል ለዚህ ደግሞ በውይይት የመፍታት ልምድ ማዳበር ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ከጣና ፎረም ምክክር ባለፈ የተግባር እርምጃ መውሰድ ይገባል ሲሉ ነው የመድረኩን አስፈላጊነት የገለጹት።

የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካና ውስብስብነት እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸው የአፍሪካ ቀንድ በነዳጅ፣በማዕድናት፣ ያልታረሰ መሬትና ውሃን ጨምሮ ያልተነኩ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉበት ቀጣና መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በፎረሙ ላይ ተናግረዋል።

በዚህም በቀይ ባሕር ላይ እየጨመረ የመጣው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለቀጣናው ሀገራት ስጋት መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤  በባብኤል መንደብና በሰፊው ቀይ ባሕር ውስጥ በንግድ መርከቦች ላይ እንደ አዲስ የተከፈቱ ጥቃቶች ስለመኖራቸው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ንግድ ሙሉ በሙሉ በቀይ ባሕር የተመረኮዘና የቀጣናው መሠረት መሆኗን ጠቅሰው፤ የደኅንነት ስጋቷን የማስወገድ፣ የባሕር ንግዷንና የንግድ መርከቦቿን በመጠበቅ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብና ጠንካራ ቀጣናዊ ውህደት ለማምጣት በትኩረት እየሠራች መሆኑን አስታውሰዋል።

በጣና ፎረም ላይ የተገኙት የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማህማ እንደገለጹት ጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላም፣ ደህንነትና ልማት ዙሪያ በግልጽ የሚመከርበት ነፃ የሃሳብ ገበያ ነው። በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም መገንባት የሚቻለው በአፍሪካዊ ተቋማትና አፍሪካን በመለወጥ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እየተቀያየረ ባለበት ሁኔታ የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት አፍሪካዊ ተቋማትን ማጠናከርና ቅንጅታዊ አንድነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ ከዚህ አንፃር የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላም፣ ደህንነትና ልማት ዙሪያ በግልጽ ውይይት የሚደረግበት ነፃ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

ጣና ፎረምን አስመልክቶ የተላለፉ መልእክቶች ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሁሉን አቀፍ ትብብር፣ትስስር፣ሰላም፣ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ እድገት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ ከማጉላት ባሻገር ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሔ ወሳኝ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም