የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ግልጽና ውጤታማ ውይይት የተደረገበት መድረክ ነው -የጋና ፕሬዝዳንትና የፎረሙ ቦርድ ሊቀ መንበር ጆን ድራማኒ ማሀማ - ኢዜአ አማርኛ
የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ግልጽና ውጤታማ ውይይት የተደረገበት መድረክ ነው -የጋና ፕሬዝዳንትና የፎረሙ ቦርድ ሊቀ መንበር ጆን ድራማኒ ማሀማ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦ 12ኛው የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ግልጽና ውጤታማ ውይይት የተደረገበት መድረክ መሆኑን የጋና ፕሬዝዳንትና የፎረሙ ቦርድ ሊቀ መንበር ጆን ድራማኒ ማሀማ ገለጹ።
"በአፍሪካ የሰላም መንገዶች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ ፖለቲካ ለውጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በባህርዳር ሲካሄድ የቆየው 12ኛው የጣና ፎረም ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።
የጋና ፕሬዝዳንትና የፎረሙ ቦርድ ሊቀ መንበር ጆን ድራማኒ ማሀማ በመዝጊያ መርሀ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በባህር ዳር ከተማ ለሁለት ቀናት የተደረገው ውይይት ውጤታማ ነበር ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ላደረጉልን መልካም መስተንግዶ የላቀ ክብርና ምስጋና አለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የፎረሙ ተሳታፊዎችንም አመስግነዋል።
12ኛው የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ደህነት ጉዳዮች ላይ ግልጽና ውጤታማ ውይይት የተደረገበት መድረክ እንደነበር ገልጸዋል።
በመሆኑም በፎረሙ የተገኙ ጠቃሚ ነጥቦችን ወደ ተግባር በመቀየር ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
አፍሪካ በአንድ ድምፅ እንድትናገር፣ አንድነትና ትብብር እንዲፈጠር ሰላም መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በጣና ፎረም ውይይት የተደረገባቸው ሀሳቦችን መተግበር በአሕጉሪቱ ያለውን ሙሉ አቅም ጥቅም ላይ ማዋል ነው ብለዋል።
አፍሪካውያን አስተሳሰባችን ዓለም አቀፋዊ ትግበራችን አካባቢያዊ መሆን አለበት ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም ለዜጎች ተጠቃሚነት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።