የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ የሚያኮራ ሰራዊት ነው - ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ የሚያኮራ ሰራዊት ነው - ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ
ባህርዳር፣ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የአገሩን ሉአላዊነትና የህዝቡን ደህንነት በጀግንነት በማስከበር የኖረ በመሆኑ፣ መላው ህዝብ የሚኮራበት ታላቅ የድል ሰራዊት ነው ሲሉ የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ገለፁ።
የምስራቅና የሰሜን ምዕራብ ዕዞች እስታፍ አባላት 119ኛውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀንን የድል ሰራዊት በሚል መሪ ሃሳብ በፓናል ውይይት በመኮድ ግቢ አክብረዋል።
ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ በበአሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጀግንነትንና አልሸነፍም ባይነትን ከአባቶቹ የወረሰው አኩሪ አሻራው ነው።
የዘንድሮውን የሰራዊት ቀን እያከበርን ያለነውም ሰራዊታችን የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ፣ ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና ዳር ድንበር ለማስከበር አኩሪ ድል እየተጎናጸፈ በሚገኝበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በዚህም በዓሉ ሲከበር አገራችን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና በዘመናዊ ስልጠና የዳበረ የመከላከያ ሰራዊት እንዳላት ለማሳየትና ለመስገንዝብ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገጸዋል።
ይህም የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ ተላላኪ ጽንፈኞች በመተባበር የሚፈጽሙትን የፖለቲካ ሴራና የሚፈጥሩትን ግጭት ቀድሞ ለማምከን የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ በአየር፣ በባህር፣ በምድርና በሳይበር ደህንነት ሰራዊታችን ትልቅ አቅም በመገንባት ለማንኛውም ተልእኮ ዝግጁ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።
ሰራዊቱ ከሀገሩ አልፎ በሰላም ማስከበር በተለያዩ የአፍሪካና በሌሎች የውጭ ሀገራት በመሰማራት ወንድማማችነትንና ሰብአዊነትን የገነባ ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ጽንፈኞችን በማጥፋት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ለሚካሄደው ፈጣን ሀገራዊ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚሰጠንን ወታደራዊ ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁነታችን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊና ሌተናል ኮሎኔል ይስሃቅ ኢና በበኩላቸው፤ የሀገራችንን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር ከጥንት ጀምሮ እስካሁን በርካታ መስዋዕትነት ተከፍሏል ብለዋል።
እኛም የመከላከያ ቀንን ዛሬ ስናከብር በቀጣይ ለሀገሪቱ ሰላምና ሉአላዊነት መከበር የሚሰጠንን ግዳጅ በጀግንነት ለመወጣት ቃል በመግባትና ለላቀ ግዳጅ በመዘጋጀት ነው ብለዋል።
"በዓሉን የምናከብረው በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ችግር የሚፈጥሩ ጽንፈኞችን በመደምሰስ የሀገር አንድነትን በማፅናት ነው" ያሉት ደግሞ የምስራቅ ዕዝ ስታፍ አባል መቶ አለቃ ሮቤል ፈቃዱ ናቸው።
በፓናል ውይይቱ ላይ የሰራዊቱ ከፍተኛና መካከለኛ መኮንኖችና አባላት ተሳትፈዋል።