በመደመር እይታ፡ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እየቀየረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር እይታ፡ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እየቀየረ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት ለሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት መለወጥ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር ፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቀ ርዕይ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ይፋ የሆነው «የሌማት ትሩፋት» መርሃ ግብር፣ ኢትዮጵያን ከምግብ ሸማችነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያለመ ታላቅ ኢኒሼቲቭ ነው።
ይህ መርሃ ግብር የከተማ ግብርናን በማስፋፋት ከተሞች በምግብ ምርት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በተለይም በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ጫና በማቃለል ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በመደመር መንግሥት ትኩረት የተሰጠው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር ላይ ይገኛል።
መርሃ ግብሩ የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆን ችሏል ብለዋል።
የከተማ ግብርናን ከከተማ ልማት ጋር በማቀናጀትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በመቻሉ፣ በግለሰብም ሆነ በተቋማት ደረጃ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ይህም ዜጎች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረጉም በላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በከተማ ግብርና ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት በእንስሳትና በእጽዋት ልማት ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ የምርታማነት እድገት ማስመዝገብ ተችሏል።
በዚህም ቀደም ሲል 200 ሺህ ቶን የማይደርስ የነበረውን አጠቃላይ ምርት ወደ 615 ሺህ ቶን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ይህም አምራቾች የቤተሰባቸውን ፍጆታ ከመሸፈን አልፈው ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የከተማ ግብርናን የበለጠ በማስፋፋት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በሚገኘው ደጃዝማች ወንዲራድ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ካሱ ቱምሳ፣ የተቀናጀ የከተማ ግብርና በትኩረት መተግበር ከጀመረ ወዲህ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ከተገኘው አዎንታዊ ውጤት የተነሳ የምርት ተጠቃሚነቱን ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ አልፎ ለአካባቢው ነዋሪ ማቅረብ መቻሉን እና ይህም ህብረተሰቡን በእጅጉ ደስተኛ ማድረጉን ተናግረዋል።
በሌማት ትሩፋት የሥራ ዘርፍ የተሰማሩት ዶክተር ንጉሴ ወልደስላሴ በበኩላቸው፣ ጥራት ያለው የዶሮ ሥጋ፣ እንቁላል እና ወተት ለአዋቂዎችና ለሕፃናት በማቅረብ እራሳቸውንም ሆነ ነዋሪውን ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን አስረድተዋል።
በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ዳንኤል ጌትዬ፣ ላለፉት አራት ዓመታት በሥራው በመቆየት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ ማሻሻል እንደቻሉ አብራርተዋል።
የተቀናጁ የከተማ ግብርና ልማቶች በየደረጃው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የኑሮ ደረጃ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።