የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚ በመቀየር ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ይሠራል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚ በመቀየር ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ይሠራል
ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚ በመቀየር ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እንደሚሠራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።
በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ የሕዝብ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያከናወናቸው ተግባራት የሕዝቦችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው።
በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም የሕዝቡን የማደግ ፍላጎት የሚመጥን ውጤት ለማስመዝገብ ከሕዝቡ ጋር የጋራ ርብርብ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ከተለያዩ የኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጸጋዎችን ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚ በመቀየር ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የክልሉ መንግሥት አመራር ቀን ከሌሊት እንደሚተጋም አረጋግጠዋል።
ለአንድ አካባቢ ዕድገት የሕዝቦች አብሮነትና አንድነት ወሳኝ በመሆኑ፣ ብዝኃነትን ባከበረ መልኩ በክልሉ እየታየ ያለውን አበረታች ውጤት እናጠናክራለን ብለዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቤንች ሸኮ ዞን የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የዘገዩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ድጋፍና ክትትል እንደሚጠናከርም ጠቁመዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኮጁ በዳካች በበኩላቸው፣ ሕዝባችንን በማዳመጥ ክፍተቶችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።
ዞኑ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመቀየር የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ የመደመር መንግሥት ኢኒሼቲቮች ተጠናክረው እንደሚተገበሩ ጠቁመዋል።
መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ቀልጣፋ የሕዝብ አገልግሎት ለሕዝቡ ለመስጠት የተጀመሩ የዲጂታል አገልግሎት ተግባራት ይጠናከራሉ ነው ያሉት።
በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው የሕዝብ ውይይት መድረክ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ከቤንች ሸኮ ዞን ሁሉም መዋቅሮች የተወጣጡ አመራሮችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።