ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በጽናት እና በጀግንነት የተወጣ የድል ሠራዊት ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ) ፦የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በጽናት እና በጀግንነት እየተወጣ የመጣ የድል ሠራዊት ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

119ኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሀሳብ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ እየተከበረ ይገኛል።

በመርሀግብሩ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣የጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የቀድሞ የሠራዊቱ አመራሮች፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎቾ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።


 

የሠራዊት ቀን የመከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ መልኩ ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም የተመሰረተበትን ታሪክ በማሰብ ይከበራል።

ቀኑ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ሚኒስትር የሰየመችበትን ቀን በማስታወስ ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ይዘከሩበታል።

ዓላማውም የሠራዊቱን ጀግንነት፣ ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ሚና እና ታላቅ አኩሪ ታሪክ ለትውልድ በቅብብሎሽ ማስተላለፍ ነው።

የመከላከያ ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የህዝብ አለኝታ የቁርጥ ቀን ጋሻ ነው።

ሠራዊቱ በርካታ ፈተናዎችን በጽናት እና በጀግንነት የተወጣ የድል ሠራዊት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በርካታ ማዕበሎችን ተሻግራ ወደ ታላቅነቷ እየገሰገሰች እንደምትገኝ አብራርተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የእድገት ጉዞ በጉልህ እየደገፈ መሆኑን ተናግረው፤ ሠራዊቱ ከውስጥ እና ከውጭ የተሸረቡ ሴራዎችን በማክሸፍ የሀገር ዳር ድንበር እና የህዝቡ ሰላም እንዲጠበቅ ማድረጉን ተናግረዋል።


 

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሁለንተናዊ አቅም በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የቀጣናውን ሰላም በማረጋገጥም አለኝታነቱን በተግባር እያስመሰከረ መሆኑን አስረድተዋል።

ማንኛውንም ትንኮሳ ማክሸፍ የሚችል የሀገር ዋስትና መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣናው ባሉ ጂኦ ፖለቲካዊ ለውጦች ምክንያት የሠራዊቱ ሚና ከምን ጊዜውም በላይ ወሳኝ ሆኖ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም