በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የእንጦጦ ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማት አካል የሆነው፣ ከቀጨኔ በአምባሳደርና በኢሬቻ እስከ ባምቢስ የተዘረጋው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ዋና ዋና ውጤቶች፦ - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የእንጦጦ ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማት አካል የሆነው፣ ከቀጨኔ በአምባሳደርና በኢሬቻ እስከ ባምቢስ የተዘረጋው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ዋና ዋና ውጤቶች፦
ከቀጨኔ በአምባሳደርና በኢሬቻ እስከ ባምቢስ የተዘረጋው ይህ ፕሮጀክት 351 ሄክታር ስፋትና 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን፣ የተለያዩ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችንና የሕዝብ መገልገያዎችን አካትቷል።
የተፈጥሮና የአካባቢ ጥበቃ
የአፈርና የውሃ ጥበቃ፣ የወንዝ ማጽዳት፣ የጎርፍ መከላከል፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችን ማስፋፋትና የገጽታ ማስዋብ ሥራዎች ተከናውነዋል።
ዘመናዊ የመንገድና የእግረኛ መሠረተ ልማት
• 16 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፤
• 20 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ፤
• 22 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፤
• 5 ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክ፤
• 18 የተሽከርካሪ ድልድዮች፤
• 23 የእግረኛ ድልድዮች ተገንብተው፣ ነባሮቹም ታድሰዋል።
ለስፖርት፣ ለመዝናኛና ለማኅበራዊ ትስስር የተዘጋጁ ስፍራዎች
ፕሮጀክቱ 12 የስፖርትና የጤና ማዕከላትን፣ ዘመናዊ የስፖርት ሜዳዎችን፣ ጂምናዚየሞችንና የፉትሳል ሜዳዎችን አካትቷል።
በተጨማሪም፦
• 21 የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች፤
• 15 ፕላዛዎችና አምፊ ቲያትሮች፤
• 8 ፋውንቴኖችና የውሃ ትርዒት ማሳያዎች፤
• በተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የሥራ ዕድል ፈጠራ
የከተማችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት 30 ካፌዎችና 185 ሱቆች ተዘጋጅተዋል። የባንክ አገልግሎቶችም ተካትተዋል።
በወንዝ ዳርቻው አካባቢ ለሚኖሩ ነዋሪዎች የኑሮና የአኗኗር ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ የዕደ ጥበብ ምርቶች ማምረቻ፣ ማሳያና መሸጫ ማዕከል ተዘጋጅቷል። በተጨማሪም የግብርና ምርቶችን ለማቅረብና ለመሸጥ የሚያስችል ማዕከል ተካትቷል።
የውሃ፣ የፍሳሽና የጎርፍ መውረጃ መሠረተ ልማት
የከተማ ዩቲሊቲዎችን ለማዘመንና የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቱን ለማሻሻል፦
• 6 ኪሎ ሜትር የንጹሕ ውሃ መስመር፤
• 11 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር፤
• 12 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መውረጃ መስመር፤
• 5 አነስተኛ ግድቦች፤
• 6 የውሃ ፍሰት መቆጣጠሪያ ግድቦች፤
• 3 የውሃ ማጣሪያ ማዕከላት ተገንብተዋል።
እነዚህ መሠረተ ልማቶች የውሃ ሀብታችንን ለመጠበቅ፣ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስና የአካባቢውን ጤናማነት ለማሻሻል ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።
ለዘላቂ ትራንስፖርትና ለአካባቢ ጥበቃ የተዘጋጁ መሠረተ ልማቶች
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ምቹ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን ለማስፋት 22 የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችና 8 የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት ተገንብተዋል። እነዚህ ማዕከላት በአንድ ጊዜ ከ100 በላይ መኪናዎችን ቻርጅ ለማድረግ ያስችላሉ።
የከተማችንን ታሪክና ባህል የሚያስተዋውቁ መገለጫዎች
የወንዝ ዳርቻ ልማት ሙዚየምና “ወደ ምንጩ መመለስ (Back to Origin)” የተሰኘው ሐውልት የከተማችንን ታሪክ፣ ባህልና የተፈጥሮ ሀብት አስፈላጊነት የሚያስተዋውቁ ልዩ መገለጫዎች ናቸው።
የልማታችን ዓላማ የሰው ሕይወትን ማሻሻል ነው!
የዚህ ልማት ዓላማ ውብ ስፍራዎችን መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ ለነዋሪው ጤናማ አካባቢ፣ የመዝናኛ አማራጮች፣ የኢኮኖሚ ዕድሎችና የተሻለ የኑሮ ሁኔታ መፍጠር ነው።