በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ዘንድሮ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ዘንድሮ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ይለማል
አዳማ ፣ጥቅምት 15/2019(ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ዘንድሮ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።
የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በመስኖ ስንዴ ልማት ለማከናወን ሰፊ ዕቅድ ተይዞ ወደ ተጨባጭ ሥራ ተገብቷል።
በዘንድሮው በጋ በዞኑ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ መስኖ በማልማት ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ገልጸዋል።
በዞኑ ያለውን የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ ሀብት በመጠቀም በመስኖ ሰፊ መሬት ለመሸፈን በማቀድ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።
የአዋሽ ወንዝን ጨምሮ የለሙ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በመጠቀም የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ መስፍን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የውሃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉንም አመልክተዋል።
በተለይ ቀደም ብሎ በአርሶ አደሩ እጅ የነበሩትንና አዳዲስ የውሃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችን ተደራሽ በማድረግ በተቀናጀ መልኩ ልማቱን ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን ጨምረው ገልጸዋል።
የምርትና ምርታማነት ማሳደጊያ ግብዓት በተለይ የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ በሚፈልገው ልክ እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ዕቅዱን ለማሳካትም ልማቱን በኩታ ገጠም፣ በሜካናይዜሽን፣ ተመሳሳይ በሆነ ቴክኖሎጂና የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በመጠቀም እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ለዚህም አርሶ አደሩ በየዕለቱ በእርሻ ማሳ በባለሙያዎች ከተደገፈ የማሳ ዝግጅት ጀምሮ ተገቢውን የክህሎት ሥልጠናና ተከታታይ ሙያዊ ድጋፍ እያገኘ መሆኑንም አብራርተዋል።
በዚህም በየደረጃው የሚገኙ የዞኑ አመራሮች፣ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሙያተኞችና የልማት ጣቢያ ሠራተኞች የዕለት ተዕለት ድጋፍና ክትትል የማድረግ ሥራን በትኩረት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በዞኑ ቦራና ዱግዳ ወረዳዎችን ጨምሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ማሳዎችን በዘር የመሸፈን ሥራ መጀመሩን አቶ መስፍን ጨምረው ገልጸዋል።