ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦ ዛሬ፣ የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀው ለአገልግሎት ማብቃታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት የ351 ሄክታር አጠቃላይ ስፋት እና የ10 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለውን የኮሪደር ልማት ዘመናዊ፣ አረንጓዴ እና ሁሉንም አካታች የሆነች አዲስ አበባን የመገንባት ራዕያችንን እውን የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የእግረኛ መንገዶችን፣ የብስክሌት መንገዶችን እና የተቀናጁ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን ያካተተ በመሆኑ፣ ይህ ልማት ይበልጥ ተደራሽ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ የከተማ ከባቢን ይፈጥራል ሲሉም ገልጸዋል።
የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ፕላዛዎችና አምፊ ቲያትሮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ እንዲሁም የውሃ ትርዒት ማሳያዎች ለመዝናኛና ማህበራዊ ግንኙነት አዳዲስ ዕድሎችን ያበረክታሉም ብለዋል።
የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እና ከ100 በላይ መኪኖችን በአንድ ጊዜ መሙላት የሚያስችሉ ስምንት የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ማዕከላት የዘመናዊ መሠረተ ልማቱን አቅም ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።
በወንዝ አስተዳደር፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ እንዲሁም በወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ስፍራዎች አማካኝነት የአካባቢ ጥበቃን ከከተማ ገፅታ ለውጥ ጋር እያቀናጀን እንገኛለን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ባስተላለፉት መልእክትም በተመሳሳይ መልኩ ይህ ልዩ የኮሪደር ልማት አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን መፍጠር ያስቻለ ነው ያሉት።
የተዘጋጀው የገበያ ማዕከል ቀደም ሲል በወንዝ ዳርቻው አካባቢ ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የዕደ ጥበብ ምርቶችን እንዲያመርቱ፣ ለማሳያና ለመሸጫ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ሲሆን፣ የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከ ደግሞ የግብርና አምራቾችን ከገበያው ጋር ያገናኛል ብለዋል።
የእኛ ርዕይ ለዛሬውና ለሚቀጥሉት ትውልዶች ውብ ብቻ ሳትሆን ምርታማና ሁሉንም አካታች እንዲሁም ህዝቧን የምትመጥን ከተማ መገንባት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልእክት።