ቀጥታ፡

ዓለም የሚጠብቀው 265ኛው የኤል ክላሲኮ ደርቢ፤ ድል ለማን?

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ):- በስፔን ላሊጋ የ10ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ በካምፕ ኑ ስታዲየም ይካሄዳል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ባርሴሎና በ27 ነጥብ በአንደኝነት ሲመራ፣ ሪያል ማድሪድ በ21 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ባርሴሎና እስካሁን ያደረጋቸውን ዘጠኝ ጨዋታዎች አሸንፏል።

በእነዚህ ጨዋታዎች 39 ጎሎችን ሲያስቆጥር፣ 9 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል።

ሪያል ማድሪድ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ሸንፈት አስተናግዷል።

23 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 9 ግቦች ተቆጥረውበታል።

የሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ታሪካዊ ተቀናቃኝነት ከ124 ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው። ሁለቱ ክለቦች እ.አ.አ በ1902 ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ባርሴሎና 3 ለ 1 አሸንፏል።

ቡድኖቹ በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 264 ጊዜ ተገናኝተዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በተመሳሳይ 106 ጊዜ አሸንፈዋል። 52 ጊዜ አቻ ወጥተዋል። በጨዋታዎቹ ላይ ባርሴሎና 440፣ ሪያል ማድሪድ 450 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

በላሊጋው 192 ጊዜ ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ 80 ጊዜ ሲያሸንፍ ባርሴሎና 78 ጊዜ አሸንፏል። 35 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

በአስደናቂ ብቃት ላይ የሚገኘው ባርሴሎና ካሸነፈ ከማድሪድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋል።

ማድሪድ ድል ከቀናው የነጥብ ልዩነቱ ወደ ሶስት ዝቅ ይላል።

ራፊኒሃ፣ ላሚን ያማል እና ፔድሪ ከባርሴሎና፣ ኪሊያን ምባፔ፣ ጁድ ቤሊንግሃም እና ቪኒሸስ ጂኒየር ከሪያል ማድሪድ በጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

የ44 ዓመቱ ሁዋን ማርቲኔዝ ሙኑዌራ ተጠባቂውን የደርቢ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም