የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦ የ2019 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ጅማሮውን ያገኛል።
ከቀኑ 8 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከይርጋጨፌ ቡና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2018 ዓ.ም የውድድር ዓመት በ69 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ሻምፒዮን መሆኑ የሚታወስ ነው።
ይርጋጨፌ ቡና በ2018 የውድድር ዘመን በ19 ነጥብ 12ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለፉትን ስድስት ተከታታይ የሊግ ውድድሮች ጨምሮ በአጠቃላይ ዘጠኝ ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል።
ቡድኖቹ ባለፈው የውድድር ዓመት በሊጉ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ንግድ ባንክ አሸናፊ ሆኗል።
በሌላኛው መርሐ ግብር መቻል ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሀዋሳ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 8 ሰዓት፣ ሲዳማ ቡና ከአዲስ አዳጊው ጉለሌ ክፍለ ከተማ ጋር ከቀኑ 10 ሰዓት በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ በወንጂ ስታዲየም እና አዲስ አዳጊው ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ከሸገር ከተማ በማሰልጠኛ ማዕከሉ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ነገ ይቆያል።
በውድድሩ ላይ 14 ክለቦች ተሳታፊ ናቸው።