አፍሪካ የዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ተቀባይ ብቻ መሆኗ አብቅቶ የገዛ እድሏን የመወሰን ጠንካራ ድምፅ ሊኖራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ የዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ተቀባይ ብቻ መሆኗ አብቅቶ የገዛ እድሏን የመወሰን ጠንካራ ድምፅ ሊኖራት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ተቀባይ ብቻ መሆኗ አብቅቶ የገዛ እድሏን የመወሰን ጠንካራ ድምፅ ሊኖራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
12ኛው የጣና ፎረም በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የብሩንዲ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ፣ የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ዳኒኤል ቻፖ፣ የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ኪቱሬ ኪንዲኪ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲ ፣ የቀድሞ የሀገር መሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ እንኳን ወደ የሰው ልጅ መገኛ ኢትዮጵያ እና ወደ አባይ መነሻ ባህር ዳር በደህና መጣችሁ ሲሉ ገልጸዋል።
የጣና ፎረም ስለ አፍሪካ ደህንነት እና ጸጥታ ግልፅ ውይይት የሚደረግበት እና በአህጉራዊ ጉዳይ የሚያሰባስብ መድረክ መሆኑን አመልክተዋል።
ዘንድሮ የተመረጠው መሪ ሀሳብ የኢኮኖሚ ጫናዎችን እና የጂኦፖለቲካዊ ለውጦችን ተቋቁሞ መቆም የሚችል ዘላቂ ሰላምን እንዴት መገንባት እንችላለን? የሚል ዋና ጥያቄ ያዘለ መሆኑን አመልክተዋል።
ሁሉንም ውጫዊ ድንገተኛ ጫናዎች መቆጣጠር ባንችልም፣ ውስጣዊ የመቋቋም አቅማችንን ግን ማጠናከር እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ የወደፊት እድሏን የሚቀርጹ ህጎችን በማውጣትና በመወሰን ሂደት ላይ ጠንካራ ድምፅ ሊኖራት እንደሚገባ አስምረውበታል።
ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማስፈን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ግጭትና ጦርነት በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ችግር እና መከራ ጠንቅቀን እናውቃልን ብለዋል።
የእኛ የመጀመሪያ እና ዋነኛ ግዴታ ዜጎችን መጠበቅ እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማስከበር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በተመሳሳይ ጊዜ ከኃይል እና ከጥቃት እርምጃዎች ወደ ፖለቲካዊ ውይይት የሚያመራው መንገድ ሁልጊዜ ክፍት መሆኑን አመልክተዋል።
የሰላም ውይይትን ለመረጡ ወገኖች በሙሉ፣ እንደተለመደው፣ ሁልጊዜም በተዘረጋ እጅ እና በክፍት ልብ ለመቀበል ዝግጁ ነን፣ እንቀበላቸዋለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
ይህ የሰላም መንገድ ደግሞ ህዝቡ ሊተማመንባቸው በሚችላቸው የፍትህ ተቋማት ላይ የተመሰረተ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አካሄዱም የዚሁ ጥረት አካል እንደሆነ ገልጸዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ የተዘጋጁት የውሳኔ ሃሳቦች ለፓርላማ እና ክልል መንግስታት የተረከቡ ሲሆን፣ አሁን ያለው ዋና ተግባር እነዚህን ሃሳቦች ወደ ውሳኔ፣ ውሳኔዎቹንም ወደ ተግባራዊ እርምጃ መለወጥ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ መሪነት የሚካሄዱ የሰላም ድርድሮች ተመሳሳይ ትምህርት አስተምረውናል፤ ስምምነት ማለት ሰላም የሚጀምርበት ቦታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሰላም ዘላቂ ሆኖ የሚቀጥለው ግን ተደራዳሪ ወገኖች የገቡትን ቃልኪዳን እና ግዴታ ሲያከብሩ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።
የእኛ ትልቅ ምኞት ዘላቂ ብልፅግናን ማምጣት ነው ብለዋል።
ኢኮኖሚያዊ ሉአላዊነት ያንን የወደፊት ተስፋ እንድንገነባ ይረዳናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም በምናመርተው ምርት፣ በምንሰበስበው ገቢ እና ውስብስብ ስርዓቶችን የመምራትና የማስተዳደር አቅማችን ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።
በምርጫ በተመረጠው የመደመር መንግስት፤ አንድነትን እንገንባለን፣ አብዝተን እናመርታለን፣ የራሳችንንም ምርጫዎች ራሳችን እንወስናለን፣ የሀገራችንንና የአህጉራችንን ስልጣኔ ወደፊት የምናስቀጥለውም በዚህ መንገድ ነው ብለዋል።
እንደ አፍሪካ ሀገራት አቅሞችንና ብቃቶችን አስተባብረን አንድ ላይ መጠቀም አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ባለሀብቶችና የንግድ ማህበረሰቦች በአህጉራቸው ስራ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።