ቀጥታ፡

የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል የክትባትና የተለያዩ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-መንግሥት የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል የክትባትና የተለያዩ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር ስለሺ ጋሮማ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

የጤና ሚኒስቴር የዓለም የፖሊዮ ቀንን “ፖሊዮን ጨርሶ ማጥፋት፤ በተለዋዋጭ ዓለም በጋራ እንድንቆም የሚያደርግ ጉዳይ” በሚል መሪ ሃሳብ በቼቫሊየር ኢትዮጵያ መናገሻ የተሃድሶ ማዕከል አክብሯል።

ፕሮፌሰር ስለሺ ጋሮማ በዚህ ወቅት፤ መንግሥት የሕፃናት ጤናና ደኅንነት በማስጠበቅ የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል የክትባትና የተለያዩ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

የፖሊዮ በሽታን በመከላከል፣ በሕፃናት አቅም ማጎልበቻ፣ በበሽታ ቅኝትና አሰሳን በማጠናከር ከጎረቤት አገሮች ጋር በድንበር ላይ በትብብር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የፖሊዮ በሽታን በመከላከል ያከናወነችው ውጤታማ ተግባርም በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖሊዮ በሽታ ክስተት ቅነሳ ተምሳሌት እንዳደረጋት አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ የጤና እክሎችን መከላከል የሚያስችሉ ከ13 በላይ ክትባቶችን ለሕፃናት፣ ለታዳጊ ሴት ልጆችና ለአዋቂዎች በመሰጠት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የፖሊዮ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት ተጋላጭ የማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ባለባቸውና የድንበር አካባቢዎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

የዓለም የፖሊዮ ቀን ሲከበርም የጤና ዘርፍ ተዋናዮች የሕፃናትን ጤንነት ለመጠበቅ ቅንጅታዊ ሥራዎችን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በተለይም የፖሊዮ በሽታ ቅድመ መከላከል የክትባት መርሃ ግብር ተደራሽነትን በማስፋት ተጋላጭነትን ማስቀረት የሚያስችል ትብብር ማጎልበት አለብን ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የጤና ሥርዓትና ፖሊሲ አማካሪ ዶክተር ቢጆይ ናምቢያር በበኩላቸው፤ ልጆችን ከፖሊዮ በሽታ ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዓለም ፖሊዮ ቀን ሲከበር የሕፃናትን ጤንነት ለመጠበቅ ከምን ጊዜውም በላይ ባለድርሻ አካላት ያለንን ቅንጅታዊ ሥራ ለማጠናከር በመነሳሳት ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሕፃናትን ጤና ለመጠበቅ ፖሊዮ በሽታን ለመከላከል የምትወስዳቸው ሀገራዊ እርምጃዎች የሚበረታቱ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም