ቀጥታ፡

‎ሀዋሳን ለኑሮ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ምቹ ከተማ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል 

‎ሀዋሳ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-ሀዋሳን ለኑሮ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ምቹ ከተማ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ። 

በከተማዋ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቁርጠኝነት በመፍታት የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 2ኛ ዙር፣ 11ኛ የሥራ ዘመን 25ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

‎የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት፣ ሀዋሳ ከተማን በማስዋብ ለኑሮ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ምቹ ከማድረግ ባለፈ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ።

በ2018 በጀት ዓመት በመሠረተ ልማት ዘርፍ አዳዲስ የልማት እሳቤዎችን ተግባራዊ በማድረግ ከተማዋን ውብና አረንጓዴ ከማድረግ ባለፈ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ሳቢነቷን የሚያጎሉ በርካታ ሠራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለይም በተለያየ ዙር የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ፣ የቱሪስት መስህብነቷን ይበልጥ ያጎሉና ከተማዋን ያዘመኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ከተማዋ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ሥርዓት እንዲኖራት፣ የወጣቶችና ሕፃናት ስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲስፋፉ፣ በርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።

በአሁን ወቅት በፍጥነት እየተከናወነ ያለው የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻና ሌሎች የኮሪደር ልማት ሥራዎች በፍጥነት፣ በጥራትና የከተማዋን እድገት በሚመጥን መልኩ ለማከናወን ትኩረት መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡

የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ትርጉም ባለው መልኩ መፍታት ሌላው ትኩረት መሆኑን ያነሱት ከንቲባ ጥራቱ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የአዳዲስ መንገድ ከፈታ፣ የመዋቅራዊ ፕላን ሥራዎችና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ሥራዎችም ይከናወናሉ ብለዋል።

ዛሬ በተካሄደው መደበኛ ጉባኤ አዲስ የተሾሙት የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ጴጥሮስ ጫማ በበኩላቸው፣ ከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ምክር ቤቱ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ በማድረግ በኩልም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንደሚወጣ ነው የገለጹት።

ምክር ቤቱ በከተማዋ በ2019 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ተግባራት ማስፈጸሚያ ከ13 ቢሊዮን 294 ሚሊዮን ብር በላይ  በጀት ያጸደቀ ሲሆን የተለያዩ ሹመቶችንም ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም