ቀጥታ፡

ታሪክ የአሁኑን ማንነት የሚቀርጽ የወደፊት ጉዟችንን የሚያበራ ህያው ኃይል ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-ታሪክ የአሁኑን ማንነት የሚቀርጽ፣ የወደፊት ጉዟችንን የሚያበራ ህያው ሃይልና የተሻለ ማህበረሰብን የሚያንጽ ድርሳን ነው ሲሉ  የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሙዚየም ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ምንይል ታዬ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

የዓድዋን ታሪካዊ ድል እና የአባቶቻችንን ገድል ለመዘከር፣ እንዲሁም የታሪክ አደራን ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለመው ሁለተኛው ሕዝባዊ ውይይት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።


 

የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች በታደሙበት በተካሄደው መድረክ የጦር ሜዳ የውጊያ ስልትን ከዲፕሎማሲ ጥበብ ጋር ባስተባበሩት ታላቁ አርበኛ ራስ መኮንን ወልደሚካኤል (አባ ቃኘው) የጀግንነትና የአመራር ዐሻራ ላይ ያተኮረ ነው።

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሬ፤ በመድረኩ የራስ መኮንን ወልደሚካኤልን የሕይወትና የጀግንነት ታሪክ የተመለከተ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል።


 

በጽሑፋቸውም፤ ታሪክ ለአንድ ሕዝብና ሀገር ወሳኝ ድልድይ ሲሆን፣ ታሪኩን የተገነዘበ ትውልድም አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ አይደለም ብለዋል።

ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የጦር አዛዥ ሆነው በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ድል የተቀዳጁ፣ ከጦር አመራር ችሎታቸው በተጨማሪ ብቁ ዲፕሎማትና ብዝሃነትን እንደ ጸጋ የሚያምኑ እንደነበር አስታውሰዋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሙዚየም ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ምንይል ታዬ ፤ ታሪክ የአሁኑን ማንነት የሚቀርጽ፣ የወደፊት ጉዟችንን የሚያበራ ሕያው ኃይል ነው ብለዋል።

ስለሆነም ታሪክ ትናንትን የሚያስታውስ ክስተት ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬን ኃላፊነት ለመገንዘብና ለነገ የተሻለ ማኅበረሰብ ለመገንባትም የሚያግዘን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የታሪክ ትውስታን የሚጠብቅ ስፍራ ብቻ ሳይሆን፣ የምርምር፣ የትምህርት፣ የማኅበራዊ ውይይት እና የፓን አፍሪካኒዝም ማስተባበሪያ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር መኳንንት ጥላሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መድረኩ የታሪክ መማማሪያና የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚያጎለብት የወል ትርክት መገንቢያ ነው ብለዋል።

መድረኩ ኢትዮጵያውያን ከቀደምት አያቶቻቸው ተምረው ሉዓላዊነታቸውንና አንድነታቸውን እንዲያጸኑ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

መድረኩ በየወሩ ከሚዘጋጀው የ“ዓድዋ ካላንደር” ጋር የተገናኙ ታሪካዊ ክንውኖችን እና ጀግኖችን መሠረት ያደረጉ መርሃ ግብሮች እያዘጋጀ መሆኑንና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።


 

ታዋቂው ፓን-አፍሪካዊ ምሁር ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ እንዳሉት፤ የውይይት መድረኩ ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ታሪክ በሚገባ እንዲገነዘብ የሚያደርግ ነው።


 

ሌላኛዋ የውይይት ተሳታፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሙላቷ ወልዴ በበኩላቸው፤ ለወጣቶችና ለመጪው ትውልድ ታሪካቸውን እንዲገነዘቡ የሚያስችል የእውቀት ሽግግር ነው ብለዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ልጅ ኤርሚያስ ተሰማ እንዳሉት፤ ውይይቱ የቀደምት አባቶችን ታሪክ ለመገንዘብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት ተማሪዎች አማኑኤል ተስፋዬና መክፊራ ከድር በበኩላቸው፤ ከአባቶቻቸው ታሪክ በመገንዘብ ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ትምህርት የሚያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም