ቀጥታ፡

የአፍሪካን የግብርና ምርታማነት ለማሻሻል ያለመ አህጉራዊ የፖሊሲ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-የአፍሪካን የግብርና ምርታማነት በውጤታማ ፖሊሲና ምርምር ለማላቅ ያለመ አህጉራዊ ጉባኤ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

ከጥቅምት 16 እስከ 18 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደውን ጉባኤ አስመልክቶ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትና የአፍሪካ የግብርና ፖሊሲ ምርምር ተቋማት ኔትወርክ (ANAPRI) የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በጉባኤውም የአፍሪካን የግብርና ምርታማነት ማነቆ፣ ከፍተኛ የማምረቻ ወጪና የግብርና ምርቶች እሴት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራዊ መፍትሔዎች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የአፍሪካ የግብርና ፖሊሲ ምርምር ተቋማት ኔትወርክ ዳይሬክተር ደሳለኝ ቤኛ (ዶ/ር) በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች ብለዋል።

በጉባኤውም በኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴና በተለያዩ ወቅቶች የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል ያስመዘገበቻቸውን ተምሳሌታዊ ስኬቶች በተሞክሮነት እንደምታቀርብ ገልጸዋል።

ከጥቅምት 16 እስከ 18 2019 ዓ.ም በሚቆየው ጉባኤ የአፍሪካን ግብርና የሚያሻሽሉ የጥናትና ምርምር ጽሑፎች የሚቀርቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአፍሪካ የግብርና ፖሊሲ ምርምር ተቋማት ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አንቶኒ ቻቡቶ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የአህጉሪቷን የግብርና ምርታማነት ለማሻሻል የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጉባኤውም ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የግል ባለሀብቶች፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በአፍሪካ ግብርና ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።

በመድረኩም የአህጉሪቱን የንግድ ትስስርና የግብርና-ምግብ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ማሳለጥ፣ በግብርና ውስጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምና የፖሊሲ ጉዳዮች የሚዳሰሱ መሆኑን አመልክተዋል።

የግብርና ድጎማዎች፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ በጉባኤው ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድና ጥናቶች እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።

ለአፍሪካ የግብርና ችግሮች በአፍሪካውያን መረጃና በጠንካራ አህጉራዊ ተቋማት መፍትሔ የመስጠት አቅምን የሚያጠናክር ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ እንደሚደረግ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተተገበረ ባለው «የሌማት ትሩፋት» ኢኒሼቲቭ ያመጣቸው ውጤቶችም በተሞክሮነት እንደሚዳሰሱ አመልክተዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የሚወጡ ጥናቶችና ውይይቶች የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ልማት፣ የኤክስቴንሽን፣ የገበያና የትራንስፖርት ተደራሽነት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ግብዓት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም