ቀጥታ፡

በክልሉ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት ይጠናከራሉ

ዲላ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና ትራንስፎርሜሽን ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከጌዴኦ ዞን እና ከዲላ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ዛሬ በዲላ ከተማ መክረዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን በማረጋገጥ ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት በትኩረት ይሰራል። 

በዚህም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የተኪ ምርቶች አቅርቦትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ግብ መያዙን ነው ያስታወቁት።

ይህን ለማሳካትም በቤተሰብ ደረጃ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በቁልፍ የልማት ዘርፎች ላይ የመቶ ቀናት ዕቅድ ወጥቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል።

በተለይም ለምግብ ዋስትና መሰረት የሆነ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራ እንዲሁም ቡናና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች  ብዛትና ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። 

ከተሞችን ውብና ጽዱ የማድረግ ጥረት እድገታቸውን እያፋጠነ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የተጀመሩ የኮሪደር ልማቶች መጠናከር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

ዕቅዱን እውን ለማድረግ የማህበረሰቡ፣ የምርምር ተቋማትና አጋር አካላት ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የህብረተሰብ ተወካዮች በበኩላቸው ከመደመር መንግሥት ጎን በመቆም የተያዙ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት  የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ተስፋዬ ባንጦሪ እንደገለጹት፣ በጌዴኦ ዞን ለቡና ልማትና ግብይት በተሰጠው ትኩረት እሳቸውን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል።

የክልሉ መንግሥት ቡናን ጨምሮ በተለያዩ የግብርና ሥራዎች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያከናወናቸው ውጤታማ ተግባራት በቀጣይም መጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡

የመንገድ መሰረተ ልማቶች መሟላት የአርሶ አደሩን ምርት በፍጥነት ወደገበያ ለማምጣት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ረገድ በክልሉ የተጀመሩ ሥራዎች በቀጣይም እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።

በዞኑ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት አውታሮች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ተጨማሪ ሥራዎች ያስፈልጋሉ ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አሰፋ ተስፋዬ ናቸው።

በክልሉ የግብርና ልማትን ከማሳደግ ባለፈ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፣ የዞኑን ሁለንተናዊ ልማት ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የንግዱን ማህበረሰብ የወከሉት አቶ የሱፍ ጠሃ በበኩላቸው፤ መንግሥት የንግድ ሥርዓቱን በማዘመኑ ፍትሃዊ የግብር አከፋፈል ሥርአት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።

በዲላ ከተማ የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም