የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተልእኮ የመፈፀም አቅሙና ዝግጁነቱ የሚያኮራ ነው- የቀድሞ ሰራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተልእኮ የመፈፀም አቅሙና ዝግጁነቱ የሚያኮራ ነው- የቀድሞ ሰራዊት አባላት
ጎንደር ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):- በዘመናዊ መልኩ የተገነባው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተልእኮ የመፈፀም አቅሙና ዝግጁነቱ የሚያኮራ መሆኑን የቀድሞ ሰራዊት አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን "የድል ሰራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በነገው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
እለቱ ሲከበር የሰራዊቱ ጀግንነትና ለሀገር የሚከፍለው ዋጋ የሚዘከርበት እንዲሁም አጠቃላይ ወቅታዊ አቋሙ በአደባባይ የሚታይበት ይሆናል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በጎንደር ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ ሰራዊት አባላት በዘመናዊ መልኩ የተገነባው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተልእኮ የመፈፀም አቅሙና ዝግጁነቱ የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሀገር አልፎ ለሌሎች አገራት ሰላም በማስከበር ከበሬታን ያተረፈው ሰራዊት በሰራዊት ቀን ውለታው መወሳቱ፣ ክብርና ምስጋና መስጠቱ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የቀድሞ የሰራዊቱ አባል ብርሀኑ በለጠ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገሩ አልፎ ለሌሎች አገሮች የሰላም ዋስትና የሰጠ ጀግና ሰራዊት መሆኑን አንስተዋል።
በዘመናዊ መልኩ የተገነባው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተልእኮ የመፈፀም አቅሙና ዝግጁነቱ የሚያኮራ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ሰራዊት ተገቢውን ክብር መስጠትና ምስጋና ማቅረብ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የቀድሞ ሰራዊት አባል ገብሬ ሞገስ፤ ኢትዮጵያ በገነባችው ዘመናዊ ሰራዊት እና ለሀገር እያደረገ ባለው የላቀ አስተዋፅኦ ሁላችንም ኮርተናል ሲሉ ተናግረዋል።
የሀገራችንን ዕድገት የማይፈልጉ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ደቅነውት የነበረውን ፈተና በማክሸፍ በጀግንነት ለሚፈፅመው ሀገር የመጠበቅ ተልእኮ ክብርና ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።
በመሆኑም የሰራዊቱ ቀን ሲከበር ለሀገር እየተከፈለ ላለው ዋጋ ክብርና እውቅና በመስጠት ልናመሰግነው ይገባል በማለት ገልጸዋል።