የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብርን የማስጠበቅ ተልዕኳችንን አጠናክረን ቀጥለናል -የሠራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብርን የማስጠበቅ ተልዕኳችንን አጠናክረን ቀጥለናል -የሠራዊት አባላት
ጅማ ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):- የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብርን የማስጠበቅ ተልዕኳችንን አጠናክረን ቀጥለናል ሲሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት ገለጹ።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ኃላፊ ኮሎኔል ሌቺሳ መገርሳ እንደገለጹት፣ ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የኢትዮጵያን ክብር የማስጠበቅ ተልዕኮውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
በዚህም ከሕዝቡ ጋር በጋራ የመቆም ቁርጠኝነቱን በተግባር እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
የሠራዊቱና የሕዝቡ ትስስር ለሀገር ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የሠራዊት ግንባታ የጽሑፍ ዝግጅት ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል አርጋው ለገሠ በበኩላቸው፣ ሠራዊቱ የሕዝቡን ሰላምና የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን በጀግንነት የመመከትና የኢትዮጵያን ክብር የማስጠበቅ ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የሀገር ኩራትና መከታ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬም የተሰጠውን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባል አሥር አለቃ ሜላት አቢዩ በበኩላቸው፣ ወታደር መሆን ከፍተኛ ኩራትና ደስታ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራችንን ከማንኛውም ስጋት ለመጠበቅና ዳር ድንበሯን ለማስከበር በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ ነን ያሉት አሥር አለቃ ሜላት የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሠራዊቱ ታላቅ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።