አምራች ኢንዱስትሪዎች የሠራተኞቻቸውን የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ማስጠበቅ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኢንዱስትሪዎች የሠራተኞቻቸውን የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ማስጠበቅ አለባቸው
ደብረ ብርሃን፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች የሠራተኞቻቸውን የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት በማስጠበቅ ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው ከሚገኙ የኢንዱስትሪ የሥራ ሃላፊዎች ጋር በሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ላይ ተወያይቷል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት ደብረ ብርሃንና አካባቢዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ማዕከል እየሆኑ መጥተዋል።
በከተማዋና አካባቢዋ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ጥራትና ብዛት ያለው ምርት በማምረት ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ኢንዱስትሪዎቹ ምርታማነታቸውን በማሳደግ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል አሠሪዎች የሠራተኞቻቸውን ደህንነትና ጤንነት ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ ስቡሕ ገበያው (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ሀይል ለኢንዱስትሪዎች በማፍራት ለምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገው መምጣቱን አመልክተዋል።
እየታየ ያለው የኢንዱስትሪዎች ምርታማነት ዘላቂ እንዲሆን ባለሀብቶች የሠራተኞቻቸውን የሥራ ላይ ጤንነትና ደህንነት መጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመው፣ ይህንን ሃላፊነት በማይወጡት ላይ ቢሮው ርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንዳሉት በደብረ ብርሃን ከተማ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ።
የፋብሪካ ሠራተኞች ተረጋግተው እንዲሰሩ በአስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፣ አሰሪዎችም የሥራ ላይ ደህንነትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ግብአቶችን ማሟላት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከፌቤላ መኪና መገጣጠሚያ የመጡት ወይዘሮ ሐይማኖት ቢችል በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የሥራ ላይ ደህንነትን ማስጠበቅ ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆን አሰሪ ድርጅቶችንም የሚጠቅም ነው።
የሮራንክ ቢዝነስ አክሲዮን ማህበር ተወካይ አቶ ተስፋዬ ሙሉ በበኩላቸው፣ አሠሪዎች ምርታማነታቸው የሚያድገው ከሠራተኞቻቸው ጋር ተግባብተውና ደህንነታቸውን ጠብቀው መስራት ሲችሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አይተንፍሱ ፀጋው፤የክልሉ መንግስት እንደዚህ ያለ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ተነጋግሮ በመፍታት ጤናማ የማምረት ሂደት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የክልሉና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የሥራ ሃላፊዎች፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ ተወካዮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።