ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ለሉአላዊነቷ መከበር የትኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ለሉአላዊነቷ መከበር የትኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን
ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ለሉአላዊነቷ መከበር የትኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ እዝ ጠቅላይ መምሪያ ወታደራዊ መኮንኖች ገለጹ።
የዘንድሮው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን በነገው ዕለት "የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ይከበራል።
እለቱን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ወታደራዊ መኮንኖች፤ በኢትዮጵያ አሁን የተገነባው ሠራዊት እጅግ ዘመናዊና ለየትኛውም ተልዕኮ የተሟላ ዝግጁነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በዕዙ የጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊ ኮሎኔል የሽዋስ ደምሴ፤ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለመዳፈር ለሚደረግ የትኛውንም የባንዳ እና የባዳ እንቅስቃሴ ሠራዊቱ የማይታገስ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከህዝቡ የወጣ ለህዝብ የቆመና ለሀገር የሚሰራ ጀግና እና ጠንካራ ሠራዊት መሆኑን አንስተው በሁሉም ረገድ የተሟላ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ለሉአላዊነቷ መከበር የትኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የዕዙ ባልደረባ ሻምበል አስራት ባሻ፤ ኢትዮጵያ አንድነቷን፣ ሰላሟንና ሉአላዊነቷን የሚያስጠብቅላት ጀግና አጥታ አታውቅም አሁንም የሀገር ጋሻና መከታ የሆነ አስተማማኝ ሠራዊት አላት ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሰላም በማፅናት ክብሯንና ሉአላዊነቷን ለማስከበር በተሟላ ዝግጁነት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላኛው የዕዙ ባልደረባ መቶ አለቃ ይዲዲያ አክሊሉ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያን በአስተማማኝ መልኩ የሚጠብቅ ብቁ እና ጠንካራ ሠራዊት ተገንብቷል ብለዋል።
በመሆኑም ለየትኛውም ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ሲሉ አረጋግጠዋል።