ቀጥታ፡

ሠራዊቱ የሀገር ባለውለታና የጽናት ተምሳሌት ነው

ጂንካ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት ሲል ውድ ሕይወቱን የሚገብር የሀገር ባለውለታና የጽናት ተምሳሌት መሆኑን በጂንካ ከተማ የሚገኙ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት ገለጹ።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን "የድል ሥራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ ነገ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የቀኑን መከበር አስመልክቶ ኢዜአ በጂንካ ከተማ ያነጋገራቸው የቀድሞ የሠራዊት አባላት፣ መከላከያ ሠራዊቱ በመስዋዕትነት ጭምር የሀገርን ነጻነት አስጠብቆ የቆየ የሀገር መከታና አለኝታ መሆኑን ተናግረዋል።   

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የቀድሞ የሠራዊት አባል ሳጅን ደኢደቆ አበራ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ዳር ድንበርን በማስከበር ዝናን ያተረፈ የኩራት ምንጭ መሆኑን አንስተዋል።

በሠራዊቱ ውስጥ ከ25 ዓመታት በላይ ማገልገላቸውን ገልጸው፣ የበኩር ልጃቸውም የሳቸውን ፈለገ ተከትሎ ሀገሩን እንዲያጸና መርቀው መላካቸውንና የሠራዊቱ አባል በመሆኑም ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

ሀገርን ማገልገል ከምንም ነገር በላይ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት ዘርፍ ውጤታማ በመሆን ለሀገሩ ቀናኢነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል።

የመከላከያ ቀን በየዓመቱ መከበሩ የሠራዊቱን ጀግንነት ከማውሳት ባለፈ ትውልዱ ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ የሚከፈልን መስዋዕትነት በአግባቡ እንዲረዳና ፍቅሩን እንዲያጎለበት ያደርጋል ብለዋል፡፡

ሠራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነት፣ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በጀግንነት ጸንቶ የዘለቀ የሀገር ኩራት እና አለኝታ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የቀድሞ ሠራዊት አባል ሀምሳ አለቃ ተፈራ ወርቁ ናቸው።

በዘመናት የተፈተነው ሠራዊታችን ለውጭ ባዳ እና ለውስጥ ባንዳ አንዴም ሳይበገር ጸንቶ በመቆም ከሀገር አልፎ ለምስራቅ አፍሪካና ለቀጣናው ሀገራት ሰላም መጠበቅ ዋስትና መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም የሀገር ኩራትና ተምሳሌትነቱን ዛሬም ድረስ አጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ሀምሳ አለቃ ተፈራ፣ በዓለም የሰላም አስከባሪነት ስሙ በቀደምትነት የሚነሳ ጠንካራ ሰራዊት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ይህን ሚናዋን በማጠናከር ዛሬም በሰላም ማስከበር ጠንካራ ተሳትፎና ጉልህ ሚና እንዲኖራት ጠንካራና ዘመናዊ ሠራዊት በመገንባቷ ኩራት እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል።

የሠራዊታችን ጀግንነት በጦር ሜዳ በሚያስመዘግበው ድል ብቻ ሳይሆን የልማት አርበኛና የበጎነት ተምሳሌት በመሆን ጭምር ነው ያሉት ደግሞ የቀድሞ ሠራዊት አባል ሀምሳ አለቃ ሉቃስ ሉሀወራቆ  ናቸው።

ሠራዊቱ ከታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪዎችና ከአውሬ ጋር እየታገለ ደምና አጥንቱን ከስክሶ ሀገር ያፀና  የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ በመሆኑ ሁሌም ክብርና ምስጋና በመስጠት ከጎኑ መሰለፍ ይገባናል ብለዋል።  

የቀድሞ ሠራዊት አባል በመሆን ለሀገርና ለህዝብ በማገልገላቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ገልፀው፣ ዛሬም የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ሲል በጀግንነት ዋጋ እየከፈለ ያለውን ሠራዊት ማክበርና ማመስገን ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም