ቀጥታ፡

በክልሉ  የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል -  ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተጀመረውን ስራ በማጎልበት የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በሆሞሻ ወረዳ ከ250 ሄክታር በላይ መሬት ላይ እያለማ የሚገኘውን የበቆሎ፣ አኩሪአተር እና ሌሎች የሰብል አይነቶችን ጎብኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ተረጂነትን ለመቀነስ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች እየተተገበሩ ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለግብርና ስራ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሁሉም አካባቢዎች የእርሻ ማሳን በመለየት እና በማልማት ለሰው ሰራሽ እና ለተፈጥሮ አደጋ የምግብ እህል ክምችት መያዝ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል ብለዋል።

ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተጀመረውን ስራ ከመደበኛ እርሻ ስራ በተጨማሪ በመስኖ ስራ መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ይህም ኮሚሽኑ ተጨማሪ የገቢ አቅም እንዲያገኝ እና የጀመረውን የእርሻ ስራ በዘመናዊ መንገድ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያግዛል ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሐመድ አብዱላዚዝ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በራሱ አቅም በሆሞሻ እና አቡራሞ ወረዳዎች ላይ ከ300 ሄክታር በላይ ማሳ እያለማ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንሼቲቩ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን በማልማት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም ክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን አቅሙ እያደገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም