ከታሪካዊ የተጋድሎ ስኬት እስከ አቪዬሽንና የሳይበር ቴክኖሎጂ የበላይነት - ኢዜአ አማርኛ
ከታሪካዊ የተጋድሎ ስኬት እስከ አቪዬሽንና የሳይበር ቴክኖሎጂ የበላይነት
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአንድ ሀገር የሉዓላዊነት ምሰሶ፣ በድንበር አካባቢ ለጠላቶቹ የእሳት ነበልባል እና ለሕዝቦች ደህንነት አስተማማኝ ደጀን ነው። የወታደራዊ ተቋማት መጠናከርና ዘመናዊነት የሀገርን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ህልውና አስተማማኝ ከማድረጉም በላይ ዓለም አቀፋዊ የኃይል ሚዛን ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚያስችል አቅም ይፈጥራል።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊትም በብዙ ዘመናት ታሪካዊ ተጋድሎ እና በውጭ ወራሪዎች ላይ ባስመዘገባቸው አንጸባራቂ ድሎች ስመ ገናና ነው። በሕዝባዊ መሠረቱ ላይ የተገነባ ፅናት ሕያው ማኅተሙ ተደርጎ የወሰዳል።
በደማቅ የወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪኩ እንደሚመሰክረው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የድል ብስራቶችን እያስመዘገበ እዚህ ደርሷል። ከዓድዋ የድል አድራጊነት ስሜትና ሀገር ፍቅር ተነሥቶ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም በተለያዩ የአፍሪካና የዓለም ሃገራት ላይ በተከናወኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያሳየው ከፍተኛ ሙያዊ ሥነ-ምግባርና ሰብዓዊነት የሀገሪቷን ስምና ዝና በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ አድርጎታል።
ዛሬ ዘመኑ የሚጠይቀውን ፈጣን የጦርነት ባህሪ ለውጥ፣ የቴክኖሎጂ ዕድገትና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተለዋዋጭነትና ስጋቶችን ለመቋቋም የቀድሞ የውጊያ ስልቶችና አደረጃጀቶች በቂ ባለመሆናቸው፣ ተቋሙ በመደመር መንግስት በተሰጠው ትኩረት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጥልቅና አጠቃላይ ተቋማዊ ሪፎርም አካሂዷል።
👉ተቋማዊና ሕዝባዊ መዋቅር
የአንድ ወታደራዊ ተቋም ጥንካሬና አቅም የሚለካው በጦር መሣሪያ ብዛት ብቻ አይደለም፤ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም በሚመራበት ዶክትሪን፣ በሚገነባው የሀገራዊ አንድነት ማዕቀፍ እና በሕዝባዊነቱ ጭምር ነው። በአሁኑ ወቅት የሃገር መከላከያ ሠራዊት ባካሄደው ጥልቅ ተቋማዊ ሪፎርም ሕብረ ብሄራዊ ገጽታ በመያዝ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆን ችሏል። ዛሬ በሕዝባዊነትና በሀገር ፍቅር ላይ የተመሠረተ ፅኑ መሠረት ገንብቷል።
ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳና ለሕገ-መንግሥቱና ለሀገር ህልውና ብቻ ታማኝ የሆነ ሙያዊ ሠራዊት ሆኖ የተደራጀ ሲሆን፤ ይህንን አቅም ከፍ ለማድረግም ሀገራዊ የጥቃት መከላከል አቅምን ለማሳደግ፣ ፈጣን ዝግጁነትን ለመገንባትና ዘመናዊ ውጊያዎችን በብቃት ለመምራት የሚያስችል አዲስ ወታደራዊ ዶክትሪን ቀርጾ ወደ ተግባር ገብቷል።
👉የአየር፣ የባህር እና የምድር ኃይል ዘመናዊነት
በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ የበርካታ የውጊያ መስኮች ውህደት ለድል ቁልፍ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንም በዚህ ረገድ አስደናቂ አቅም ላይ ደርሷል። በቅርብ ጊዜያት ባደረገው የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ተሃድሶ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመናዊ የውጊያ ኤርክራፍቶችን፣ የትራንስፖርትና የደህንነት አውሮፕላኖችን እንዲሁም የተራቀቁ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) በመታጠቅ የአየር ክልሉን ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ማድረግ ችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ሀገራዊና ቀጣናዊ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን በዘላቂነት ለማስከበር የቀድሞውን ታሪካዊ የባህር ኃይል በዘመናዊ አደረጃጀት፣ በሰለጠነ የሰው ኃይልና በላቀ የቴክኖሎጂ ስልጠና እንደገና ማደራጀት ተችሏል።
👉የሳይበር፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የመረጃ መረብ አቅም
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ ውጊያ ከተለመደው የምድርና የአየር ስልቶች አልፎ ወደ ሳይበርና መረጃ መረብ ዓለም በሰፊው ተሸጋግሯል፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንም ይህንን ነባራዊ እውነታ በመረዳት የቴክኖሎጂ የበላይነትን ሙሉ በሙሉ ለመጎናጸፍ ከፍተኛና ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን ወስዷል።
በዚህም መሠረት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዙ ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያ፣ የጠላት እንቅስቃሴ በቅርበት መከታተያ እና የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ተዘርግተው በስራ ላይ ውለዋል። ከዚህም ባሻገር በሀገራችን ስትራቴጂካዊ መሠረተ-ልማቶችና በወታደራዊ የመረጃ መረቦች ላይ የሚቃጡ ማንኛውንም ዓይነት የሳይበር ጥቃቶች በቅጽበት የመከላከል፣ የመመከት እና የሉዓላዊነት ደህንነትን የማስጠበቅ የላቀ ብቃት በከፍተኛ ደረጃ ተገንብቷል።
👉የወታደራዊ ሳይንስ የትምህርትና ምርምር ተቋማት
አንድ ዘመናዊ ሠራዊት ዘላቂነቱና አስተማማኝነቱ የሚረጋገጠው በራሱ የትምህርትና የቴክኖሎጂ ምርምር ተቋማት ጠንካራ መሠረት ላይ ሲደገፍ ነው። በዚህ ረገድ እንደ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ፣ የመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የመከላከያ አዛዥና ስታፍ ኮሌጅ ያሉ የላቀ ሙያዊ ማሰልጠኛዎች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠነ ብቁ መኮንን እና ወታደራዊ አመራር በማፍራት ላይ ይገኛሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የሀገር ውስጥ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር ወታደራዊ መሣሪያዎችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት፣ የመጠገን እና የማሻሻል አቅም ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መጥቷል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትናንት በጀግንነት፣ በፅናትና በደም ያስከበረውን የሀገር ሉዓላዊነት፤ ዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በበቃ የሰው ኃይል፣ በጠንካራ ወታደራዊ ዶክትሪንና በፅኑ ተቋማዊ ሪፎርም አስደግፎ በማስቀጠል ላይ ይገኛል።
ይህ የታሪክ ጉዞና አሁናዊ የዘመናዊነት ደረጃ የሚያሳየው፣ መከላከያ ሠራዊታችን ለሀገር ሰላምና ህልውና ታማኝ ዘበኛ፣ ለሕዝቦች ደህንነት ደግሞ አስተማማኝና የማይበገር ደጀን መሆኑን ነው። መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን በአጭር ጊዜ በስኬት የሚወጣ የጀግንነት አርማ ነው።