ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚስተዋሉ ተለዋዋጭ የደህንነት ስጋቶች በአፍሪካውያን የጋራ ትብብር እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚስተዋሉ ተለዋዋጭ የደህንነት ስጋቶች በአፍሪካውያን የጋራ ትብብር እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እየሠራች እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ 12ኛው ከፍተኛ የአፍሪካ ደህንነት ጉባኤ የሆነው ጣና ፎረም የልማት ተምሳሌት በሆነችው ውቢቷ ባህርዳር መጀመሩን አመልክተዋል።


 

መድረኩ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ለማፍለቅ፣ በአፍሪካውያን የሚመሩ ዘላቂ የሰላም ሂደቶችን ለማበረታታት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

አፍሪካ በመደመር እሳቤ በሀገር በቀል እሴቶችና በጋራ የመፍትሔ ፍለጋ መርሆ በመመስረት ችግሮቿን በራሷ ልጆች፣ በራሷ እሴቶች፣ በራሷ እውቀትና ጥበብ የምትፈታበትን መንገድ ለማመላከት ጣና ፎረም ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

የጣና ፎረም በውቢቷ ባሕርዳር የጣና ሐይቅ ዳርቻ መካሄዱ፣ የከተማዋን አህጉራዊ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅምና ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ለሚስተዋሉ ተለዋዋጭ የደህንነት ስጋቶች አፍሪካውያን በጋራ መቆም አለባቸው የሚል ፅኑ አቋም በመያዝ በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም