ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት አካታች ምኅዳር አብሮነትና አንድነትን በማጎልበት የሀገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን ጉልህ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-የመደመር መንግሥት አካታችና አሳታፊ ሁለንተናዊ ምኅዳር አብሮነትና አንድነትን በማጎልበት የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና ለማፋጠን ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ምሁራን ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

የመደመር መንግሥት የካቢኔ ስብጥርና አካታችነትም የኢትዮጵያን ሕብረብሔራዊ አንድነት የሚያስጠብቅ እና የሕዝብ ውክልናን ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ ፖሊሲና ጥናት ኢንስቲትዩት የማኅበራዊ ልማትና አካታችነት ማዕከል ኃላፊና ከፍተኛ ተመራማሪ ደሳለኝ የሺሰው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የመደመር መንግሥት የካቢኔ ስብጥር የኢትዮጵያን መልክ የሚመስል ነው። 

የመደመር መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የኢትዮጵያን የልማትና የዕድገት የፖሊሲ ፍኖት በመቅረጽ በስኬት ማስተግበር በሚያስችል መልኩ የተዋቀረ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የካቢኔው አካታችነትም የሁሉንም ዜጎች ሀገራዊ ባለቤትነት በማንጸባረቅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እኩል የመወሰን ዕድልን የሚያጎናጽፍ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ አካል መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህም ዜጎች ለመንግሥት የልማትና ዕድገት የፖሊሲ አቅጣጫ ተፈጻሚነት ተሳትፎን በማላቅ ለጋራ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት መተማመንን የሚያጎለብት መሆኑን አመላክተዋል። 

የመደመር መንግሥት የሴቶች የካቢኔ ቁጥር ከፍተኛ ተሳትፎም የሁሉም የሆነችና ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለመሥራት ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል። 

የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በየደረጃው በሚገኝ የመንግሥት አስፈጻሚነት የኃላፊነት ቦታ መመደባቸውም አዲስ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ባህል ልምምድ መሆኑን አስረድተዋል። 

ይህ አዲስ የፖለቲካ ባህልም የሐሳብ ብዝኅነትን በማስፋት የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ለማስፋት የሚያስችሉ ሀገራዊ የፖሊሲ ሐሳቦችን አፍልቆ ለመተግበር ጎላ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል። 

ወጣቶች በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት እርከን መካተታቸውም ለተተኪ ትውልድ ከፍተኛ የመነቃቃት አቅምን መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ዕድል መሆኑን አመላክተዋል። 

የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአመራርና አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ዑጁሉ ኮክ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት እሳቤ የሀገራችንን እምቅ ጸጋዎች ወደ ዕድል እየቀየረ ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያውያን በሕብር የተሸመነ አንድነትም የሀገርን ጸጋ ወደ ዕድል በመቀየር ወንድምና እህትማማችነትን የሚያጎለብት አስቻይ የትብብር ምኅዳር መሆኑን ገልጸዋል። 

የመደመር መንግሥት አካታችና አሳታፊ ሁለንተናዊ ምኅዳርም አብሮነትና አንድነትን በማጎልበት የሀገራችንን ዕድገትና ብልጽግና ለማፋጠን ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የተገነቡና በግንባታ ሂደት የሚገኙ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም የሀገርን ዕድገት መሻት የሚያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም