ክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለልማት የማዋል ስራ ይጠናከራል - ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለልማት የማዋል ስራ ይጠናከራል - ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)
ሙዱላ ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለልማት የማዋል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለፁ።
በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በመንግስት የልማት አቅጣጫዎች ዙሪያ ህብረተሰብ አቀፍ የምክክር መድረክ በሙዱላ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት ክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ፀጋዎች የማልማትና መልካም እሴቶችን በማጎልበት ለጋራ ተጠቃሚነት የማዋል ስራ ይጠናከራል።
የመደመር መንግሥት የአካባቢ ፀጋን ለይቶ በማልማት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ታላላቅ እቅዶችን እየተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጠምባሮ ህዝብ ችግሮችን የሚፈታበትና ሰላምና አብሮነትን የሚያጠናክርበት ባህላዊ እሴት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
አካባቢው ለግብርናና ለቱሪዝም ዘርፉ ውጤታማነት መረጋገጥ ምቹ ስነ ምህዳር ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ፀጋዎቹን ደምሮ በመጠቀም ለጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተድላ ሎምበሶ በበኩላቸው የልዩ ወረዳዉ በማር፣ በቅቤና በዓሳ ሀብት ከፍተኛ ምርት የሚገኝበት ነው ብለዋል።
አካባቢዉ በግብርናና በቱሪዝም ዘርፉ ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የማህበረሰቡን ተሳትፎ መሰረት ያደረገ አሰራር እንደሚተገበር አስታውቀዋል።
በምክክር መድረኩ ከተሳተፉት መካከል ወጣት ሎጲሶ ምናሴ እንደገለፀው የመደመር መንግሥት ለአካባቢው ልማት መሳለጥ የሚያግዙ መሰረተ ልማቶችን እያከናወነ ይገኛል።
በአካባቢው እየተከናወኑ የሚገኙ ልማቶችን ለማጠናከር ከመንግሥት ጎን ሆኖ እንደሚሰራ አመልክቷል።
ወይዘሮ ደሳለች ተስፋዬ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት ለመስራት ያሳየዉ ቁርጠኝነት የሚደገፍና መጠናከር ያለበት ተግባር ነው ብለዋል።
በአካባቢው ለልማት ስራዎች መሳለጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልል፣ የልዩ ወረዳው ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ከፍሎች ተሳትፈዋል።