አፍሪካ በራሷ ቁጥጥር ሥር የሚሆን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመገንባት የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ አለባት - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ በራሷ ቁጥጥር ሥር የሚሆን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመገንባት የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ አለባት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-አፍሪካ አቅሟን በማስተባበርና በራሷ ቁጥጥር ሥር የሚሆን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመገንባት የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ አለባት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሉዓላዊነትና የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ህልውና ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
12ኛው የጣና ፎረም የመክፈቻ መርሐ ግብር በውቢቷ ባህርዳር በጣና ሐይቅ ዳርቻ "በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ" በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል።
በአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም መፍትሔ በማፍለቅ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ የዘንድሮው የጣና ፎረም የትኩረት አጀንዳዎች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ በምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ በዓባይ መነሻዋ ባህር ዳር የተገኙ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ላይ ለመምከር ወሳኝ አፍሪካዊ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ የሚከሰቱ ሁሉንም አደጋዎች መቆጣጠር እንደማይቻል ገልጸው፤ የዜጎችን አይበገሬነት ማጠናከር ግን ከእኛ ይጠበቃል ብለዋል።
በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በመጀመሪያ የህዝብን ደኅንነት መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ግጭትን በውይይት የመፍታት ልምድ ማዳበር ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በጣና ፎረም ከምክክር ባለፈ የተግባር እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።
አፍሪካ የራሷን ሰላም በራሷ መወሰን አለባት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትኩረታችን ሕዝባችን ላይ መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሰላምና ልማትን በማስተሳሰር የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ከራሷ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እያቀረበች መሆኑን ተናግረዋል።
በቅርቡ የማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በመክፈት የአፍሪካ ማዕድናትን ለማጣራት አጋዥ ይሆናል ብለዋል።
አፍሪካ አቅሟን ማስተሳሰር እንዳለባት ገልጸው፤ ራሳችን የምንቆጣጠረው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመገንባት የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ የመደመር ኤአይ ዩኒቨርሲቲ በመገንባት ሂደት ላይ መሆኗን ገልጸው፣ ይህም አፍሪካውያንን ጭምር እንደሚያሳትፍ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሉዓላዊነትና የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ እየሰራች መሆኑን አመልክተው፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ገቢራዊ መደረግ አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ መትከሏን ገልጸው፣ ልማት ዋነኛው የሰላም መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።